በሎጂስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ በተደረገው ማሻሻያ በዓመት 50 ሚሊዬን ዶላር ወጪ ማስቀረት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በሎጂስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ በተደረገው ማሻሻያ በዓመት 50 ሚሊዬን ዶላር ወጪ ማስቀረት ተችሏል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2012 (ኢዜአ) በሎጂስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ በተደረገ ማሻሻያ በዓመት እስከ 50 ሚሊዬን ዶላር ወጪ ማስቀረት መቻሉን የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ገለጸ።
ይህም ሆኖ ድርጅቱ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ሰጪ ከሆነው 'መርስክ' ኩባንያ የ10 ሚሊዬን ዶላር እዳ እንዳለበት ተገልጿል።
በጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀው 'አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ' የውይይት መርሃ ግብር ዛሬ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ሪፎርም ላይ ትኩረቱን አድርጎ ውይይት ተደርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በታደሙበት በዚህ ውይይት የዘርፉ አንቀሳቃሾችና የመንግስት ተወካዮችም ተገኝተዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን አቶ መኮንን አበራ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ ዘርፍ በዓለም ዓቀፍ መመዘኛ መስፈርቶች ሲታይ እጅግ ዝቅተኛ ነው።
ችግሩ የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን አስመጪዎች፣ አስተላላፊዎችና ወደብ አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚፈጥሩት የተደመረ ችግር ነው ብለዋል።
ይህ በመሆኑ ደግሞ አስመጪና ላኪዎች በሰበብ አስባቡ ወደቦችንና መጓጓዣዎችን እንደ መጋዘን በመጠቀማቸው አንድ ጭነት ለማጓጓዝ እስከ ሶስት ወራት ይፈጃል ብለዋል።
ባለስልጣኑ በአመዛኙ በቅንጅታዊ አስራር ችግር ምክንያት የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
ስትራቴጂው በዘርፉ በማነቆነት የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት 98 የመፍትሄ ኃሳቦችን ያካተተ በመሆኑ ወደ ትግበራ ቢገባ የተሻለ ለውጥ ያመጣል ብለዋል።
የሎጂስቲክስ ምሁሩ ዶክተር ማቲዎስ ኢንሰርሙ ደግሞ ዘርፉ ከውጪ ምንዛሪ እጥረት ውጪ በማነቆነት የሚገለጽ ችግር የለውም ሲሉ ይሞግታሉ።
የሎጂስቲክስ ዘርፍ በቀላሉ የደንበኛውን ፍላጎት በሚያረካ መልኩ ጭነትን ከመነሻው እስከ መድረሻው ማድረስ መሆኑንም ያስረዳሉ።
በቀጣይ ኢትዮጵያን እንደ ዓለም አቀፍ ወደብ ማስተላለፊያ አድርጎ ማቀድና መስራት፣ በሁሉም የአገሪቷ አቅጣጫ የባቡር መሰረተ ልማት መዘርጋትና አሁን ያለውን ስርዓተ ትምህርት አሻሸሎ መተግበር ዋናዎቹ መፍትሄዎች ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ ዘርፍ በአገልግሎት አሰጣጡ ምንም እንኳን ዝቅተኛ ደረጃ የሚሰጠው ቢሆንም በቅርብ ዓመታት በተሰሩ ማሻሻያዎች ለውጦች ታይተዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ በቅርቡ በተደረጉ ማሻሻያዎች የተገኙ ውጤቶችን ይዘረዝራሉ።
ዘርፍን የበለጠ አቅናጅቶ ለማስኬድ በወደብ፣ በትራንስፖርት፣ በመንገድ መሰረተ ልማትና በአስተላላፊዎች በኩል ያሉትን ችግሮች ለማቃለል ተሞክሯል ብለዋል።
በዚህም አገሪቷ ከዚህ በፊት ከምታወጣው ወጪ አንጻር እስከ 50 ሚሊየን ዶላር የወደብ ወጪ ማስቀረት እንደተቻለ አብራርተዋል።
ከአጠቃላይ ጭነት ማጓጓዝ ስራው ውስጥ የኢትዮጵያ መርከቦች ድርሻ 20 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው ፤ 80 በመቶ ጭነት የሚጓጓዘው በሌሎች መርከቦች ነው ብለዋል።
በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት 'መርስክ' ለተባለው የዴንማርክ ኩባንያ ያልከፈለው የ10 ሚሊየን ዶላር እዳ አለበት ተብሏል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ዘርፉ አሁንም ውስብስብ ችግሮች ያሉበትና አስፈላጊው ትኩረት ያልተሰጠው መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሮቹን በዝርዝር አብራርተዋል።
ከችግሮቹ መካከል ዘርፍን የሚመሩ ተቋማት 24 ሰዓት አገልግሎት አለመስጠት፣ በዘርፉ ተዋናዮች መካከል የጋራ እቅድ አለመኖርና የመሰረተ ልማት ችግሮች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በውጪ ምንዛሬ ምክንያት በቂ ፋይናንስ ማግኘት አለመቻልና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ያለማዋልም ዘርፉን አንቆ ይዞታል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪና የንግድ ተደራዳሪ አቶ ማሞ ምህረቱ ''ዘርፉ ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል'' ብለዋል።
ዘርፉ ኢኮኖሚን ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያግዝ ፣ የስራ ዕድል የሚፈጥርና የገቢ ምንጭ በመሆኑ ትኩረት ማግኘቱንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በሎጂስቲክስ ዘርፍ አፈጻጸም ደረጃ ከ160 አገራት በ128ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን መረጃዎች ይጠቁማሉ።