የኮንትሮ ባንድ ንግድ በህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ጫና እየፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮንትሮ ባንድ ንግድ በህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ጫና እየፈጠረ ነው
ሁመራ የካቲት 27/2012 (ኢዜአ) የኮንትሮባንድ ንግድ እየተበራከተ በመምጣቱ በስራችን ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረብን ነው ሲሉ የሰቲት ሁመራ ከተማ ህጋዊ ነጋዴዎች ቅሬታ አሰሙ ።
በሰቲት ሁመራ ከተማ በጅምላ ንግድ ስራ የተሰማሩ አቶ አማን ዕቁባሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት ለአንድ ጥቅል የላስቲግ እሽግ የለስላሳ መጠጥ በህጋዊ መንገድ ገዝተው በ380 ብር ሂሳብ ለቸርቻሪዎች እንደሚያከፋፍሉት ተናግረዋል።
በህገ ወጥ መንገድ በሱዳን በኩል ወደ ከተማው የሚገቡ እሽግ የላስቲግ መጠጦች ደግሞ እስከ 80 ብር ቅናሽ በሆነ ዋጋ እንደሚሸጡ ገልጸዋል።
በህገ ወጥ መንገድ ወደ ከተማው የሚገቡ ምርቶች በአንፃራዊ መልኩ የዋጋ ቅናሽ ስለሚታይባቸው ህብረተሰቡ ከህጋዊ ነጋዴዎች እንዲሸሹ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።
አቶ የማነ ገብረክርስቶስ የተባሉት ጅምላ አከፋፋይ በበኩላቸው ከአዲስ አበባ የሚያመጡቱን ሮል የዱቄት ሳሙና አምስቱን ኪሎ ግራም በ250 ብር ሂሳብ ለቸርቻሪዎች የሚያቀርቡ ቢሆንም ከሱዳን የሚገባው ግን አምስቱን ኪሎ ግራም የዱቄት ሳሙና በ170 ብር ሒሳብ እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል ።
የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው የተዛባ የገበያ ውድድር እንዲኖር በማድረግ በግብር ከፋይ ህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫና ማሳደሩን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል ።
በኢትዮጵያ ጉምሪክ ኮሚሽን የሰቲት ሁመራ ቅርንጫፍ የኮንትሮማንድ ክትትልና እርምጃ አወሳሰድ ቡድን መሪ ምክትል ኢንስፔክተር ተፈራ ታደሰ በጉዳዩ ላይ እንደተናገሩት ባለፉት ስድስት ወራት 17 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።
ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ12 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ገልፀው ህጋዊ ንግዱን እየጎዳው መሆኑን ትክክል ነው ብለዋል ።
ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የተያዙ የኮንትሮማንድ እቃዎች የጥራት ማረጋገጫ የሌላቸው መድሀኒቶች፣አደንዛዠ እጾች፣የሺሻ መገልገያዎች ጭምር እንደሚገኙባቸው ተናግረዋል።
ለአገር ውስጥ ግብይት እንዲያገለግል ፍቃድ ያልተሰጠው 550 ሺህ የሌላ አገር የብር ኖትና እሽግ የለስላሳ መጠጦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ።
የጉምሩቅ ስርአት ሳይከተሉ ከአገር ሊወጡ ሲሉ የተያዙ የቁም እንስሳትና ጤፍና ቅመማ ቅመም የመሳሰሉ ምርቶች ጭምር ተይዘዋል ።
የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ከአከባቢው የቆዳ ስፋት ጋር ተያይዞ አስቸጋሪ እንዳደረገው ቡድን መሪው ገልፀው ያም ሆኖ ግን አቅም በፈቀደ መጠን ህብረተሰቡን በማሳተፍ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል ።
በኮሚሽኑ የሰቲት ሁመራ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ኮማንደር መሰለ ይመም በበኩላቸው አሁን የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት በህጋዊ ነጋዴዎች ላይ እያጋጠመ ያለውን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ለመግታት የተቀናጀ ስራ እንደሚከናወን ገልፀዋል ።
የሰቲት ሁመራ ንግድ ኢንዱስቱሪና ከተማ ልማት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ዳንአኤል ጸጋይ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው የንግዱ ማህበረሰብ ያነሳው ቅሬታ ትክክል መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የአቅርቦት እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት በብዛት በኮንትሮማንድ የገቡ እቃዎች ገበያ ላይ እንደሚውሉ ተናግረዋል።
ጽህፈት ቤቱ ክትትል በማድረግ የኮንትሮማንድ እቃዎች ይዘው በተገኙ 63 ነጋዴዎች የቅጣት እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል።