ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿን በፍትሃዊነት እየተጠቀመች በመሆኑ በየትኛውም መመዘኛ ተጠያቂ ልትሆን አትችልም

የካቲት 27/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ አባይን ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿን በፍትሃዊነት እየተጠቀመች በመሆኑ በየትኛውም መመዘኛ ተጠያቂ ልትሆን አትችልም ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።

በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ በተፋሰሱ አገሮች እስካሁን የተፈረሙ ስምምነቶች በኢትዮጵያ ላይ አስገዳጅነት የሌላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

አንድ አገር በድንበሩ ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም የመልማት ሉዓላዊ መብት አለው።ይህም መብት ዓለምአቀፋዊ ነው።

ይሁንና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሉዓላዊ አገራትን ድንበር አቋርጠው ከመሄዳቸው ጋር ተያይዞ አገሮቹ ውሃውን የመጠቀምና በውሃው የመልማት መብት ያላቸው መሆኑን የውሃ ስምምነቶች ላይ ተደንግጓል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ በድንበሯ ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶቿን በመጠቀም ህዝቦቿን ከድህነት ለማውጣት ጥረት ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ከአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ አባይን ጨምሮ ሌሎችንም ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ስትጠቀም የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የአለምአቀፍ የውሃ አጠቃቀም መመዘኛዎችን መስፈርት የሚያሟላና አገሪቱን ተወቃሽ የማያደርግ ነው ብለዋል ባለሙያዎቹ።

የታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች በተለይ የአባይ ወንዝ ላይ ኢ-ምክንያታዊ ቅሬታና ወቀሳ ማቅረባቸው የተለመደ መሆኑን በማንሳት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና አለምአቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህርና የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከመጪው ክረምት ጀምሮ ውሃ መሙላት እንደሚጀምር ይፋ መደረጉን ተከትሎ ካለፈው ነሃሴ ወር ጀምሮ ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ለመፍጠር ሙከራ ማድረግ ጀምራለች።

ጫናው ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ከመጨረስና ሃይል ከማመንጨት የሚያስቆም አለመሆኑን ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ከጀመረች አንስቶ ለተፋሰሱ አገሮች ግልጽ መረጃን ከመስጠት ጀምሮ የወንዙን ውሃ በፍትሃዊነት ለመጠቀም ያላትን ፍላጎት በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷን ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።

ይሁንና በተለይ በግብጽ በኩል የኢትዮጵያን ልማት የሚቃወሙና የራስን ጥቅም ብቻ ያማከሉ ጥያቄዎች ማቅረቧ ኢትዮጵያን በየትኛውም የውሃ አጠቃቀም መመዘኛ ተጠያቂ የማያደርግና የግድቡን ግንባታ የማያስተጓጉል ነው ብለዋል።

ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ በአዲስ አበ ዩኒቨርስቲ ፖለቲካል ሳይንስና አለምአቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪ

ግድቡ የትላልቅ ፕሮጀክቶች መነሻ እንጂ መድረሻ አለመሆኑን አንስተው ይህም ለመንግስትም ሆነ ለተደራዳሪ ቡድኖች ከፍተኛ አቅም የፈጠረ ነው ብለዋል።

ዜጎች የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የድርሻቸውን እንዲወጡ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የምስራቅ ናይል የቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ፈቅ አህመድ ነጋሽ

የግድቡ ግንባታ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2015 ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን ካርቱም ላይ የተፈራረሙት የመርሆዎች ስምምነትም ሆነ የተባበሩት መንግስታት በ1997 ያወጣው የውሃ ድንጋጌ በማይጥስ መሆኑን ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንደማይጠናቀቁ ዓለምአቀፍ ተመክሮዎች ያሳያሉ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም በ2007 ዓ ም ይጠናቀቃል ተብሎ የተጀመረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሊዘገይ ችሏል።

በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ 71 በመቶ የደረሰ ሲሆን በ2015 ዓም እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም