ቀጥታ፡

የዓረብ ሊግ በሕዳሴው ግድብ ላይ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ የኢትዮጵያ መንግሥት አወገዘ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2012 (ኢዜአ) የአረብ ሊግ በሕዳሴው ግድብ ላይ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ቁልፍ ጉዳዮችን ሳያገናዝብ ለአንድ ወገን ያደላ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት አወገዘ። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የዓረብ ሊግ የሕግ አስፈፃሚ ካውንስል በትላንትናው ዕለት የሕዳሴውን ግድብ በተመለከተ የደረሰበት ውሳኔ የሚያሳዝን ሆኖ ያገኘው መሆኑንና ኢትዮጵያ ውሳኔውን በፍጹም የማትቀበለው መሆኑን ገልጿል።

የሱዳን መንግሥት በዓረብ ሊግ ለቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ድጋፍ ላለመስጠት የወሰደውን አቋምም ኢትዮጵያ እንደምታደንቅ በመግለጫው ተጠቅሷል።

ሱዳን የተቀነባበረውን እና የዓረብ ሊግን አቋም ባለመደገፍ የምክንያታዊነት እና የፍትሕ ድምፅ መሆኗን ዳግመኛ ማረጋገጧን በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ በመርህ ላይ ለተመሠረተው እና የሁሉም ወገን አሸናፊነትን መሠረት ላደረገው የሱዳን አቋም ወደር የለሽ አድናቆቷን ገልጻለች።

ኢትዮጵያ ከዓረብ ሊግ አገራት ሕዝቦች እና መንግሥታት ጋር በጋራ እሴት፣ ባሕል እና ልማድ ላይ የተመሠረተ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ግንኙነት እንዳላት በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

የዓረብ ሊግ የተለያዩ ሉዓላዊ ሀገራትን ያቀፈ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የሁሉንም ወገን ፍላጎት ያካተተ እና ሚዛናዊ መስመር መያዝ እንደሚጠበቅባት በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ መስመር በተቃረነ መልኩ የሚሠራ ከሆነ ግን የሊጉ ተዓማኒነት እና በዚህ እጅጉን በተሳሰረ ዓለም ውስጥ ሰላምን፣ መረጋጋትን እና ትብብርን ለማምጣት ያለው አቅሙ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ስትገልጽ እንደነበረው ሁሉ ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን "የአሁኑን እና የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት የዓባይን ውኃ ሃብት የመጠቀም መብት አለኝ" የሚለው የዘለቀ እና የማይናወጥ አቋም በድጋሚ ገልጻለች፡፡

የዓባይ ወንዝ ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆኑም ኢትዮጵያ በሌሎች ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ሳይደርስ ውኃውን በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ መንገድ የመጠቀም መርህን ተከትላ እንደምትሰራ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል እና አሠራር ላይ መሠረታዊ መፍትሔ የሚሰጠውን የመርሆዎች መግባቢያ ስምምነት ተከትላ እንደምትሠራም ማረጋገጧ ተገልጿል።

በመጨረሻም፣ የዓረብ ሊግ እውነተኛውን መንገድ ተከትሎ እና ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የዘለቀ እና የጋራ እሴቶች ላይ የተመሠረተውን ግንኙነት መሠረት በማድረግ እንደሚሠራ ኢትዮጵያ እንደምትተማመን በመግለጫው ተመልክቷል።

ወዳጅነትን ማጠናከር እና ለጋራ ግቦች ተቀራርቦ መሥራት የኢትዮጵያ የምንጊዜም ፍላጎት መሆኑም ተጠቅሷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም