ህገ-ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን ለመከላከል ዜጎች ወደ መደበኛ ያልሆነ የንግድ ስርዓት እንዲገቡ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ህገ-ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን ለመከላከል ዜጎች ወደ መደበኛ ያልሆነ የንግድ ስርዓት እንዲገቡ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ የካቲት 27/2012 (ኢዜአ) ህገ-ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን ለመከላከል ባለፈው አንድ አመት ተኩል ከ25 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ መደበኛ ያልሆነ የንግድ ስርዓት እንዲገቡ መደረጉን የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ መደበኛ ባልሆነ የንግድ ስርዓት ውስጥ ካሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በዛሬ እለት ውይይት አካሂዷል።
የቢሮው መደበኛ ያልሆነ ንግድ ስርዓት ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ሎሌ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በከተማዋ ባለፈው አንድ አመት በህገወጥ መንገድ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ከ58 ሺህ በላይ ዜጎች ተመዝግበዋል።
ከነዚሁ መካከል እስካሁን ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑት የመስሪያ ቦታ በማመቻቸትና የንግድ ባጅ በመስጠት ወደ መደበኛ ያልሆነ የንግድ ስርዓት እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።
ይህንኑ ስራ አጠናክሮ በመቀጠል በቀጣይም ቀሪዎቹን ተመዝጋቢዎች ወደ መደበኛ ያልሆነ የንግድ ስርዓት ለማስገባት ይሰራል ብለዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ግን ሌሎች አማራጭ መፍትሄዎችን መጠቀም እንጂ ይህ ብቻ በቂ አለመሆኑንም አስረድተዋል።
ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከልም ቀደም ሲል የተደራጁ አባላት የራሳቸውን ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማድረግም የውይይት መድረኩ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የመጡ በርካታ ስራ አጥ ወጣቶችን በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ የማሰማራት ስራም በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሆኖም ችግሩን በጋራ ለመፍታትና ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት እንዲቻል ክልሎች በራሳቸው አካባቢ በቂ የስራ እድል እንዲፈጥሩ ለማስቻል በጋራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ኮሚሽነር አዱኛ ደበላ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ለከተማዋ የህገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ መበራከት ዋና ምክንያት የጎዳና ላይ ነጋደዎቹ ብቻ አይደሉም።
ይልቁንም የንግድ ቁሳቁሶችን ለጎዳና ላይ ነጋደዎች በማከፋፈል በጋራ እየሰሩ ያሉ በርካታ ህገ ወጥ ተግባር የሚፈፅሙ ነጋዴዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ችግሩን ከመሰረቱ ማስወገድ የሚቻለው መደበኛ ባልሆነ መንገድ የተደራጁ ዜጎች እንዲሁም ሁሉም ህብረተሰብ በጋራ ሲንቀሳቀሱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
መደበኛ ያልሆነ ንግድ ማለት ፈቃድ ተሰጥቷቸው ቅዳሜና እሁድ አንዲሁም በባእላት ቀናት በተፈቀዱ ጉዳናዎች ላይ የሚከናወን የንግድ ስርአት ማለት ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ መደበኛ ያልሆነ የንግድ ስራን ለመምራትና ስርዓት ለማስያዝ በ2009 ዓ.ም ደንብ መውጣቱ ይታወቃል።