ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ተሳትፎ መጠናከር አመራሩ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ - ኢዜአ አማርኛ
ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ተሳትፎ መጠናከር አመራሩ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2012 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ መጠናከር በየደረጃው ያለ አመራር የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት 12ኛ መደበኛ ጉባዔውን አካሂዷል።
በጉባዔው ላይ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ደመቀ መኮንን ለግድቡ ግንባታ የተጀመረው ንቅናቄ ስኬታማ እንዲሆን በየደረጃው ያለ አመራር የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የግድቡ ግንባታ ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮ ህዝባዊ ተሳትፎው ባለፉት ዓመታትም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
"የጀመርነውን እንጨርሰዋለን ሁለት ሶስተኛው ተገባዷል ቀሪውነ እዳለፉት በጣም የተራዘመ ጊዜ ሳይጠይቅ ማጠናቀቅ በሚያስችል አገራዊ ንቅናቅ ውስጥ እንቀጥላለን፤ ይሔ ንድፈ ሐሳብ አይደለም በተግባር እዚህ ያደረሰ ሕዝብ ቀሪውን ያጠናቅቃል።መሪነት ከዚህ አኳያ በየደረጃው ያለንን ኃላፊነት መወጣት ይገባል።" ነው ያሉት።
አሁን ላይ የተጀመረውን አገራዊ ንቅናቄ በየደረጃው ያለ አመራር አደረጃጀቶችን በመጠቀም ውጤታማ ስራ እንዲሰራም አሳስበዋል።
የህዳሴ ግድብ የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክር በመሆኑ የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለፁት ደግሞ የውሃ፣ መስኖ ኢነርጂ ሚንስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ናቸው።
ኢትዮጵያ የውሃ ሀብት ማማ ብትሆንም የዝናብና የወንዞች ፍሰት ተለዋዋጭነት መኖር በሚፈለገው ልክ ውሃ እንዳይኖር አና ህዝቦቿም ለችግር እየተዳረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ህዝቦችን ከድህነት ለማለቀቅ በታችኛው የተፋሰስ አገራት ላይ ተጽዕኖ በማያስከትል መልኩ የግድቡ ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
አሁን ላይ ግድቡን በተቻለ ፍጥነት ለማስኬድ እና በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ግድቡ የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክር በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ በበኩላቸው ለግድቡ ግንበታ የተጀመረውን ህዝባዊ ተሳትፎ ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ለዚህም ሁሉም አደረጃጀት በቅንጅት ለግድቡ የሚደረገውን ድጋፍ ህብረተሰቡ አጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ መንቀሳቀስ ይገባዋል ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት 9 ዓመታት ከህብረተሰቡ 13 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል።
በዚህ ዓመትም እስካሁን 400 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ምክር ቤቱ አስታውቋል።
በ3ኛው ዙር የ8100 A የሕዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ የተጀመረ ሲሆን በመርሃ ግበሩ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዷል።