ቀጥታ፡

ሰባት የሕክምናና አንድ የፍተሻ ላቦራቶሪ የአክሪዲቴሽን እውቅና ተሰጣቸው

አዲስ አበባ የካቲት26/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን ጽህፈት ቤት ዓለም አቀፍና ብሔራዊ መስፈርቶች ላሟሉ ሰባት የሕክምናና አንድ የፍተሻ ላቦራቶሪ የአክሪዲቴሽን የምስክር ወረቀት ሰጠ።

ለተቋማቱ የተሰጠው የምስክር ወረቀት የሕክምና ላቦራቶሪ ISO 15189 ነው።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ፍስሐ እንዳሉት ተቋማቱ ባቀረቡት ማመልከቻ መሰረት በሰነዶቻቸውና በመስክ ተገምግመው ባቀረቡት የአክሪዲቴሽን ወሰን ዓለም አቀፍ እውቅና ይገባቸዋል ተብሎ  ጸድቆላቸዋል።

እውቅናውን ያገኙት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሬንሲቭ፣ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሬንሲቭ፣ የህይወት ፋና ስፔዣላይዝድ እና የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታሎች እንዲሁም ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ሴንተር እና ድሬዳዋ ሪጅናል ላቦራቶሪዎች ናቸው።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሬንሲቭ ስፔዣላይዝድ ሆስፒታል እና ሄማ ዲያግኖስቲክ አድቫንስድ ላቦራቶሪ በሁለት የፍተሻ ወሰኖች ተጠቃሚ እንደሆኑም ተገልጿል።

ጽህፈት ቤቱ በተጨማሪም ለብሔራዊ የእንስሳት ጤና ምርመራ ማዕከል በሞሎኪዩላር፣ በባክቴሪዮሎጂ እና በሴሮሎጂ የፍተሻ ወሰኖች አክሪዲቴሽን ሰጥቷል።

እንደ አቶ አርአያ ገለጻ ተቋማቱ የአክሪዲቴሽን ተጠቃሚ መሆናቸው ለህብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ይበልጥ ተአማኒነት እንዲኖረው ይረዳል።

ዜጎች ለተደጋጋሚ ወጪ እንዳይዳረጉ በማድረግ ረገድም ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ጽህፈት ቤቱ አገልግሎቱን ለማጠናከር በዓለም ባንክ ድጋፍ ከኳሊቲ ካውንስል ኦፍ ኢንዲያ ጋር በሰርቲፊኬሽን፣ ኢንስፔክሽንና ካሊብሬሽን ፕሮጀክቱን እያሰፋ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም