ቀጥታ፡

አየር መንገዱ ለቢዝነስ ተጓዦች በሚሰጠው አገልግሎት ተሸለመ

    አዲስ አበባ ሚያዝያ 26/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለቢዝነስ ተጓዞች በሚሰጠው አገልግሎት ዓለም አቀፍ ሽልማት አገኘ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅና ተቀባይነት ካላቸው የጉዞ ድረ-ገጾች አንዱ የሆነው "ትሪፕአድቫይዘር" አየር መንገዱን በ2018 "በአፍሪካና በህንድ ውቅያኖስ ለቢዝነስ ተጓዦች አገልግሎት ከሚሰጡ አየር መንገዶች ምርጥና የተሻለ" በሚል ሰይሞታል።  "ትሪፕ አድቫይዘር" ላለፉት 12 ወራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ አየር መንገዶች ዋንኛ በሚባሉት የሚጓጓዙ መንገደኞችን በማናገር ለአገልግሎት በሚሰጠው ዋጋና ጥራት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሌሎቹ የተሻለ ነው በሚል ተመርጧል።  የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ሽልማቱ ተጓዦች አየር መንገዱ እየሰጠ ላለው አገልግሎትና ለሚያቀርባቸው ምርቶች የሰጡት ከፍተኛ የመተማመኛ ድምጽ ነው ሲሉ ተናግረዋል።  አየር መንገዱ ለቢዝነስ ተጓዦች ከበረራው ጀማሮ እስከ ፍጻሜ ደንበኛን መሰረት ያደረገ የተቀላጠፈና ምቹ አገልግሎት ከመስጠቱ በተጨማሪ  ከተጓዦች ጋር ዘላቂነትና ወጥነት ያለው ትስስር አለው ብለዋል።  ለቢዝነስ ተጓዦች እየሰጠ ያለውን ምቹ አገልግሎት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አዳዲስ ቴክኖጂዎችን በሚጠቀሙት በቦይንግ 787፣ በኤርባስ 350 እና ሌሎች አውሮፕላኖች ላይ መዋዕለ-ነዋዩን እንደሚያፈስ አስታውቀዋል። አገልግሎቱን የተሻለ በማድረግ የቢዝነስ ተጓዦች ከኛ የሚጠብቁትን አገልግሎትና ተመራጭነቱን ለማስቀጠል አየር መንገዱ በትጋት ይሰራል ብለዋል።  የ"ትሪፕ አድቫይዘር" ምክትል ፕሬዚዳንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ብራያን ሳልትስበርግ እንዳሉት አየር መንገዶች በሚሰጡት አገልግሎት ተጓዦች የነበራቸውን ቆይታ በመመልከት ደንበኞች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምርጥ አገልግሎት ያገኙበት እንደሆነ እውቅና ሰጥተዋል።  ከመቼውም ጊዜ በላይ ደንበኞች አየር መንገዶች ዘላቂነትና ጥራት ያለው አገልግሎት በተሻለ መልኩ እንዲሰጧቸው እንደሚፈልጉም ተናግረዋል። ደንበኞች በሽልማቱ ከጠበቁት በላይ አገልግሎት ለሰጣቸው አየር መንገድ ትልቅ እውቅናና ውጤት መስጠታቸውን ያሳዩበት እንደሆነ ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቀናት በፊት ፓክስ ኢንተርናሽናል መጽሄት ባዘጋጀው ሽልማት የ2018 የአፍሪካ ምርጥ የምግብ አገልግሎት ሽልማት አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም