ቀጥታ፡

መንግስት ኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድብ የሚኖራትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26/2012 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአገሪቱ የሉዓላዊነት መገለጫ በመሆኑ መንግስት ይህን ክብር ለማስጠበቅ እንደሚሰራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ አስተባባሪ ምክር ቤት 12ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት አካሂዷል።

በጉባኤው የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ የምክር ቤቱ አባላት ተገኝተዋል።

በጉባኤው የግድቡ ግንባታ የደረሰበት ደረጃና የታችኛው ተፋሰስ አገራት የሦስትዮሽ ድርድርን የተመለከተ ገለፃና ውይይት ተደርጓል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአሁኑ ወቅት የግድቡ ሁለት ሦስተኛ ስራ መጠናቀቁን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ጋር በጋራ የመጠቀም እንጂ የእነሱን ጥቅም የመጋፋት ፍላጎት እንደሌላት ገልጸው፣ በግብጽ በኩል በተበዳይ ስነ-ልቦና የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እውነታንና ሀቅን ያልተከተለ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እውነትንና ፍትህን ይዛ የምትንቀሳቀስ መሆኑና የሌላውን ጉሮሮ የመዝጋት ዓላማ እንደሌላት የተናገሩት አቶ ደመቀ፤ ከተፋሰሱ አገራት ጋር የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ውይይትና ድርድር አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

መንግስት የኢትዮጵያን ክብር እና ጥቅም በማስጠበቅ በኩል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአገሪቱ የሉዓላዊነት መገለጫ በመሆኑ ይሄንንም ክብር ለማስጠበቅ እንደሚራም አቶ ደመቀ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በስሜት ሳይሆን በጥሞና እና በዲፕሎማሲ ጥቅሟን ለማስከበር ቁርጠኛ መሆኗን የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ግድቡ የትውልድና የታሪክ ጉዳይ በመሆኑ በእርግጠኝነት እንጨርሰዋለን" ብለዋል።

የውሃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ደግሞ ፤ በግድቡ ዙሪያ ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ጋር ከ2012 ጀምሮ ውይይት ሲካሄድ መቆየቱን አንስተዋል።

ከዚህ ቀደም ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ጉልህ ተጽዕኖ እንደማያመጣ የግብጽ እና ሱዳን ባለሙያዎችን ጨምሮ ከፈረንሳይ፣ እንግሊዝና፣ ጀርመን እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ የመጡ አጥኚዎች ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በቅርቡ በዋሽንግተን ከግብጽና ሱዳን ጋር የነበረውን ድርድር በተመለከተ መጀመሪያ ላይ አሜሪካ

የታዛቢነት ሚና እንደነበራት የኋላኋላ ግን አመቻች ሆና መምጣቷ፤ በኋላም ውሳኔ ሰጪ መሆኗ ትክክል እንዳልሆነም ገልፀዋል።

ሱዳን ከራሷ መብትና ጥቅም አንፃር እንጂ ለግብጽ ወግና እንዳልቆመች የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ አገሪቱ በግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ እንደሆነች እንደምታምንም ጭምር ገልፀዋል።

ጉዳዩ በውይይትና በድርድር የሚቋጭ መሆኑንና ከዚህ ውጪ ግን መንግስት የኢትዮጵያን ጥቅምና ክብር አሳልፎ እንደማይሰጥ ተናግረዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ በበኩላቸው በህዝቡ ዘንድ የተቀዛቀዘውን ስሜት እንደገና እንዲነሳሳ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በህዝቡ በኩል ፕሮጀክቱን ከዳር ለማድረስ ቁርጠኝነት እንዳለ እየታየ መምጣቱን ገልፀው ይህን ሁኔታ በሚገባ በመጠቀም ህዝቡን ማንቀሳቀስ እንደሚገባም ጭምር ነው የተናገሩት።

የህዝባዊ ተሳትፎ ብሄራዊ ምክር ቤት አባላቱ ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሉዓላዊነትና ህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ድጋፉን ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም