የዓድዋ ድል የሚዘክር ሙዚየም በዓድዋ ከተማ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል የሚዘክር ሙዚየም በዓድዋ ከተማ ተከፈተ
አክሱም፣ የካቲት 26/12 (ኢዜአ) በዓድዋ ከተማ የሚገኘው ጥንታዊ የነገስታት ቤተ መንግስት ተጠግኖ የዓድዋ ድልን የሚዘክር ሙዝየም ሆኖ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉን የከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ጽገ ተስፋማርያም ለኢዜአ እንደገለጹት የከተማው ነዋሪዎች የዓድዋ ድልን የሚዘክር ሙዚየም እንዲገነባ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
የፌዴራል መንግስት ሙዚየም እንደሚያስገነባ ቃል የገባ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ተግባራዊ ባለመሆኑ ጊዜያዊ ሙዚየም ማደራጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ለመነሻ የሚሆን ሙዚየም መክፈት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የከተማ መስተዳደሩ በሰጠው ትኩረት አፄ ዮሃንስን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው ነገስታት ሲጠቀሙበት የነበረው ቤተ መንግስት ተጠግኖ ለጉብኝት ክፍት ሆኗል።
በዓድዋ ጦርነት ወቅት ለጦር መሳሪያነት ያገለገሉ ባህላዊ ቁሳቁሶችና የጀግኖች ፎቶ ግራፎችን በማማፈላለግ ወደ ሙዚየሙ የማስገባት ስራ መጀመሩን ምክትል ሃላፊው ገልጸዋል።
እንዲሁም በግለሰቦችና በመንግስት እጅ ያሉና ከአድዋ ድል ተያያዠነት ያላቸው ሌሎች የተለያዩ ጥንታዊ መሳሪያዎች ወደ ሙዚየሙ እንዲገቡም የአካባቢው ህዝብ በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በከተማው የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ማህበር እንዲቋቋም የተደረገ ሲሆን ማህበሩ ፕሮጀክት በመቅረጽ ሙዚየሙ የማሳደግና ጥንታዊ ቅርሶችን የማሰባሰብ ስራ እያከናወነ መሆኑንም አቶ ጽገ ገልጸዋል።
የኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢ ሮ ጋር በመተባበር ቅርሶችን በማሰባሰብ ድጋፍ እንዲያደርጉም ምክትል ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
የዓድዋ ድል የሚዘክር ሙዚየም መከፈቱ ወጣቱ ትውልድ ታሪኩን በሚገባ እንዲያውቅና የቱሪስት ፍሰትን እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በሙዚየሙ በአስጎብኝነት የተሰማራው ወጣት ቴድሮስ ገብረመድህን ተናግሯል።
የአድዋ ድልና ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍና ድሉም ሁሌ እንዲታወስ ሙዚየሙ የጎላ ጠቀሜታ አለው ብሏል።
አሁን በሙዚየሙ ውስጥ በጦርነት ጥቅም ላይ የዋሉ የነገስታት የተወሰኑ አልባሳትና የተለየዩ ፎቶ ግራፎችን ተሰባስቧል ያለው ወጣቱ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች መጎብኘት መጀመራቸውን ተናግሯል።
''የከተማ አሰተዳደሩ የጀመራቸው ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዩኒቨሲቲው በገንዘብና በሙያ ደጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ''ያሉት ደግሞ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂና ቱሪዝም ኢንስቲዩቲት ዳይሬክተር አቶ ተክለብርሃን ለገሰ ናቸው።