ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማጠናቀቅ ለትውልድ የታሪክ አሻራ ማስቀመጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማጠናቀቅ ለትውልድ የታሪክ አሻራ ማስቀመጥ ነው
ጎንደር /ደብረብርሃን/ሀረር፣ 26/2012 (ኢዜ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በፍጥነት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በማድረግ ለመጭው ትውልድ የታሪክ አሻራ እናስቀምጣለን ሲሉ የዩኒቨርሲቲ ሙሁራን ተማሪዎችና ፖለቲከኞች ገለፁ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቅ ለመጪው ትውልድ የታሪክ አሻራ ማስቀመጥ መሆኑን የተናገሩት የጎንደርና የባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች መሁራን ፣ ተማሪዎች፣ የሀረሪ ክልል፣ የድሬዳዋ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን ለኢዜአ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተባበረ ክንድ በማጠናቀቅ ለወጣቱ ትውልድ የታሪክ አሻራ ልናስቀምጥለት ይገባል።
የህዳሴው ግድብ በፍጥነት ለማጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይገባል የሚል መልእክትም
አስተላልፈዋል።
በግድቡ ዙሪያ የአሜሪካኖች ቁጣና የግብፆች ፍጥጫ ግንባታውን በእልህና በወኔ እንዲፈጠን ያደርገዋል እንጂ የሚያሳድረው ነገር እንደሌለ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የህብረተሰብ ሳይንስና ስነሰብዕ ኮሌጅ ዲን ዶክተር አገኘሁ ተስፋ በበኩላቸው ግድቡ ባንድነት እንደተጀመረው ሁሉ በመላ ህዝቡ ድጋፍ በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
‹የጥንት አባቶች በጠላት ላይ የተቀዳጁት ድል ለአሁኑ ትውልድ ስንቅ በማድረግ የአባቶችን ገድል በታላቁ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ልማቶች መድገም ይገባል ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ተማሪ መሳፍንት በሪሁን እንዳለው ደግሞ የህዳሴው ግድብን በተባበረ ክንድ በማጠናቀቅ በጨለማ የሚኖሩ እናቶችን ህይወት በብርሃን ለመተካት እንረባረባለን ብሏል።
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሙሁራን በሰጡት አስተያየት ደግሞ የአሜሪካ መንግስት ጣልቃ ገብነት ከቅኝ ግዛት አስተሳብ ተለይቶ የሚታይ አይደለም።
በዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር ዶክተር አስማማው አዳነ ለኢዜአ እንደገለጹት የህዳሴው ግድብ የአገራችን ህዝቦች ከኪሳቸው በማዋጣት የገነቡት ታላቅ ፕሮጀክት ነው።
ምንም እንኳን በራሳችን የሚገነባ ቢሆንም በድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ላይ የሚገነባ በመሆኑ ሱዳንንና ግብጽን የማይጎዳ መሆኑን ለማረጋገጥ ተደጋጋሚ ድርድርና ውይይት መካሄዱ ተገቢነት ያለው ነው ብለዋል።
ነገር ገን የአሜሪካ መንግስት በታዛቢነት እንሳተፋለን ካለ በኋላ የግብጽን መብት ለማስጠበቅ ካለው ፍላጎት በመነጨ በኢትዮጵያ ላይ እያሳደረ ያለው ተጽእኖ ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብና ድርጊት ተለይቶ የማይታይ መሆኑን ገልፀዋል።
በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ ትምህርት ክፍል ሀላፊ አቶ ገንዘብ አታላይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ ህዝቦቿን በኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ የማድረግ ሃላፊነትና ግዴታ አለባት።
ተፈጥሮ የለገሰንን የአባይን ወንዝ አትጠቀሙም በማለት የሚካሄደው እንቅስቃሴ በሉአላዊነታችን ላይ ጣልቃ መግባት በመሆኑ ከቅኝ ግዛት ተለይቶ አይታይም ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀረር ከተማ በብልፅግና ፓርቲ ስልጠና ላይ የሚገኙ መካከለኛ አመራሮች ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የያዘችው አቋም የህዘብን ጥቅምና ፍላጎት ያገናዘበ በመሆኑ እንደሚደግፉት ተናግረዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ትእግስት ሙሉጌታ በሰጡት አስተያየት ግድቡ ሃብታምና ድሃ ፣ ልጅና አዋቂ ወጣትና ሴቶች ሁሉም በየአቅሙ አሻራው ያኖረበት አገራዊ ሀብት በመሆኑ አንደ ዓይነታችን ብሌን እናየዋለን ብለዋል ።
አቶ አብዱልራዛቅ መሀመድ የተባሉ አመራር በበኩላቸው የተፈጥሮ ሃብታችንን የማበልፀግና የመጠቀም ሙሉ መብት ስላለን ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የያዘችው አቋም ተገቢና የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
አመራሮቹ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።