በኢትዮጵያ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ባለመኖሩ የተፈጥሮ ኃብት ብክነት እያስከተለ መሆኑ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ባለመኖሩ የተፈጥሮ ኃብት ብክነት እያስከተለ መሆኑ ተጠቆመ
አዲስ አበባ የካቲት 26/2012 በኢትዮጵያ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ባለመኖሩ በሀገሪቱ ደንን ጨምሮ ሌሎች የተፈጥሮ ኃብቶች ለብክነትና ለጉዳት እየተዳረጉ መሆኑ ተገለጸ።
የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በተቋሙ ተግባራት ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የተዘጋጀ ስልጠና በቢሾፍቱ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይግዛው እንደገለጹት፤ አገሪቱ የተፈጥሮ ኃብቶቿን በየትኞቹ መስኮች መጠቀም ትችላለች የሚለውን ሃሳብ በግልጽ ያስቀመጠ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ የላትም።
''ይህም ባለመኖሩ ኢትዮጵያ ያላትን የደን ሃብት በአግባቡ እየተጠቀመችበት እንዳልሆነና ይህ መሆኑ ደግሞ ዘርፉ የሚፈልገውን ያህል ጥቅም እንዳይሰጥ አድርጎታል'' ብለዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያላትን መሬት ለየትኛው ተግባር ይውላል የሚለውንና እንዴት ማስተዳደር ይቻላል የሚለውን ጉዳይ የሚያሳይ አሰራር ስርዓት እንደሌለ አመልክተዋል።
በዚህ ምክንያት አገሪቷ ደንን ጨምሮ ሌሎች የተፈጥሮ ኃብቶቿን በተቀናጀ መልኩ እንዳትጠቀም ከመሆን ባሻገር ኃብቱም እየባከነ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሚዛነ ምድር ፕሮግራም አዘጋጅ አቶ እንዳለ ዘውዱ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖር ለፋብሪካ መዋል የሌለባቸው መሬቶች ለፋብሪካ ግንባታ እንዲውል ማድረጉን ጠቁመዋል።
እነዚህ መሬቶች ፋብሪካው በሚያመነጨው ተረፈ ምርቶች ለከፋ ጉዳት እየተዳረጉ መሆኑንና የቁጥጥር ሂደት ላይ ክፍተት እንደፈጠረ አቶ እንዳለ ጨምረው ተናግረዋል።
በጥቅሉ በኢትዮጵያ የትኛውን መሬት ለደን ሃብት፣ የትኛውን ደግሞ ለፋብሪካ ብሎ ለይቶ ያስቀመጠ ማዕቀፍ ባለመኖሩ የተፈጥሮ ኃብቶች ያለአግባብ እየተጎዱ መሆኑን ገልጸዋል።
የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የፖሊሲ፣ የህግና ደረጃዎች ጥናትና ዝግጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አየለ ሃጌና በበኩላቸው ''ፖሊሲው ባለመኖሩ አገሪቷ መሬቶቿን ለማህበራዊ ልማትና ለኢኮኖሚያዊ ልማት ብላ ለይታ መጠቀም አላስቻላትም'' ብለዋል።
ኮሚሽኑ ይህንን ችግር ለመፍታት ላለፉት ሁለት ዓመታት ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሮ ፖሊሲ አዘጋጅቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንደላከ ገልጸዋል።
ፖሊሲው የሚጠበቅበትን ሂደት አልፎ ሲጸድቅ አገሪቷ የመሬት ሃብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንድታውል የሚያስችላት መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።