ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የካራማራን ድል አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የካራማራን ድል አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26/2012(ኢዜአ) ጠቅላይ ሚንስትሩ መላውን ህዝብ "ከዚያድ ባሬ መራሹ የሶማሊያ ወራሪ ኃይል ጋር በነበረን ተጋድሎ ወሳኝ ድል ላስመዘገብንበት የካራማራ ድል በዓል" እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
የ1967ቱ የሶማሊያ ወረራ ሀገራችን ከአብዮት ፍንዳታው ጭጋግ ባልወጣችበትና የእርስ በርስ ግጭት ላይ በነበረችበት ጊዜ የተከሠተ መሆኑንም በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያን የወረሩ አብዛኞቹ ኃይሎች እንደሚሠሩት ስሕተት ዚያድ ባሬም ተሳሳተ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሀገር የደከመች መስሎት ኢትዮጵያን የማሸነፊያ ጊዜ የደረሰለት እንደመሰለውም ገልጸዋል።
ዚያድ ባሬ በዚህ የተሳሳተ ስሌት ተመርቶ ወረራውን ፈጸመ፤ በመጀመሪያ አካባቢ እንዳሰበውም የጎላ መከላከል ሳይገጥመው ሰፊ የሀገራችንን መሬት ማካለል ቻለ።
ነገር ግን ኢትዮጵያውያን እንደፍግ ተኝተው እንደ እቶን በተነሡ ጊዜ ምን እንደሚያደርጉ በዚአዲስ ቨህ ወረራ ጊዜ አሳዩ ብለዋል።
በአጭር ጊዜ “የእናት ሀገር ጥሪ” የተሰባሰቡ፣ በቂ የሥልጠናም ሆነ ዝግጅት ያልነበራቸው፣ ነገር ግን ከየትም የማይበደሩት የሀገር ፍቅርና የማሸነፍ ወኔ ያላቸው ውድ ኢትዮጵያውያን ወረራውን በስኬት መቀልበስ ቻሉ።
መንግሥታትን በሀገር ውስጥ ክዋኔያቸው በአንድም በሌላም ልንመዝናቸው እንችላለን።
ነገር ግን የሀገርን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የሚከፈሉ መሥዋዕትነቶች በየትኛውም ዘመን ቢፈጸሙ የሀገራችን ታሪካዊ ኩራት ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የደርግ መንግሥትም በአጭር ጊዜ ጥሪ አቅርቦ፣ አሠልጥኖና አደራጅቶ የሀገርን ክብር ለማስመለስ ያደረገው ተጋድሎና ያስመዘገው ድል የሁላችንም የኢትዮጵያውያን የአልበገር ባይነትና ለሀገር የመሥዋዕትነት የመክፈል ታሪካችን አካል ነው።
ሁሌም በውስጣችን ክፍተት ሲኖር የውጭ ጠላት እንጋብዛለን፤ ስንጠናከር ግን የታፈርንና የተከበርን እንሆናለንም ብለዋል በመልእክታቸው።
በዚህ አጋጣሚ ከኢትዮጵያውያን ጎን ተሠልፈው የተዋጉትንና ውድ ሕይወታቸውን የሠዉትን የኩባ እና የየመን ወታደሮችን ውለታ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል ብለዋል።
"ክብር ሀገርን ለማቆየት ራሳቸውን መሥዋዕት ላደረጉ ኢትዮጵያውያን" በማለት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ መልዕክታቸውን ቋጭተዋል።