የኢትዮ-አሜሪካ 2020 የንግድ ትርኢት በዋሽንግተን ዲሲ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-አሜሪካ 2020 የንግድ ትርኢት በዋሽንግተን ዲሲ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎቶች በአሜሪካ ገበያ ለማስተዋወቅ ያለመ "ኢትዮ-አሜሪካ 2020 የንግድ ትርኢት" በዋሽንግተን ዲሲ ሊካሄድ ነው።
የንግድ ትርኢቱ ከግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ከ200 በላይ የንግድ ተቋማትና ከ2 ሺህ በላይ ጎብኚዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮ ማስታወቂያ፣ ዓለም ንግድና ማስታወቂያ አገልግሎትና ዱናሚስ ሶሻል ኢንተርፕረነር ያዘጋጁትን የንግድ ትርኢት አስመልክቶ ዛሬ በአዲሰ አበባ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮ ማስታወቂያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አርቲስት አበበ ፈለቀ እንዳሉት አሜሪካ ለአፍሪ አገራት ያመቻቸችው ከታሪፍና ከቀረጥ ነፃ የገበያ እድል (አገዋ) መሰረት ከ650 በላይ የምርት አይነቶችን ወደ አሜሪካ ገበያ ማቅረብ ትችላለች።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ከውጭ እያስገባች ወደ ዓለም ገበያ የምትልከው ምርትና አገልግሎት መጠን ግን ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የምርት ጥራት ጉድለት ለውጭ ገበያ በሚቀርበው ምርት ዝቅተኛነት አንዱ ምክንያት መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ከግንቦት 13 እስከ 15 ቀን 2012 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ የሚካሄደው የንግድ ትርኢት ለዚህ አይነተኛ የምርት ማስተዋወቂያ መድረክ ይሆናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከታሪፍና ከቀረጥ ነፃ የገበያ እድል ስምምነት ህግ (አግዋ) መሰረተ 35 በመቶ ታክስ ሳትከፍል በነጻ ምርቷን ወደ አሜሪካ ማቅረብ እንደምትችል አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ አሜሪካ ያመቻቸችውን ከታሪፍና ከቀረጥ ነፃ የገበያ እድል በመጠቀም ምርታቸውን በነጻ መላክ ከሚችሉ 39 የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ መሆኗንም ገልጸዋል።
በንግድ ትርኢቱ በቆዳና ሌጦ፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በባንክና ሪል ስቴት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
የንግድ ትርኢቱ በኢምፖርትና ኤክስፖርት፣ በአገልግሎትና ቱሪዝም ላይ ያተኮረ በመሆኑ የኢትዮጵያን ገጽታ ለዓለም በማስተዋወቅ ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የኢትዮ-አሜሪካ 2020 የንግድ ትርኢት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ከኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክርቤትና ከሌሎች የመንግስትና የግል ተቋማት ጋር በትብብር የተዘጋጀ ነው።