ቀጥታ፡

የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና የኃይል እጥረት አገራቱ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ነው

አዲስ አበባ፣የካቲት 26/2012(ኢዜአ) በምስራቅና በደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና ያለው የኃይል እጥረት የአገራቱ ምጣኔ ኃብት በአህጉርና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ነው ሲል የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ዘጠነኛው የምስራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና የኃይል ተቆጣጣሪዎች ማኅበር /ራሬሳ/ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደህና እንደገለጹት በቀጣናው ያለው የኃይል አቅርቦት ችግር የአገራቱን የገበያ ተወዳዳሪነት እየጎዳው ነው።

ቀጣናው ምንም እንኳን የተፈጥሮ ሃብት የተቸረ ቢሆንም ኃይል አምርቶ በመጠቀም ረገድ እጅግ ኋላቀር  ነው ብለዋል።

በነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ የኃይል መቆራረጥ የሚያጋጥም በመሆኑ የአገራቱን አገልግሎት አሰጣጥም ጎድቶታል ነው ያሉት ዶክተር ፍሬህይወት።

ችግሩ የአህጉሪቷን 12 ነጥብ 5 በመቶ የምርታማነት ሠዓት የሚያባክን ሲሆን አሃዙ በደቡብ እስያ አገራት 7 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል።

አገራቱ የችግሩን አሳሳቢነት ተረድተው የኃይል ማመንጨትና ማሰራጨት ዕቅዳቸውን ስልታዊ በሆነ መልኩ መተግበር እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው "ያለንን እምቅ የተፈጥሮ ኃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ብናውል ነዳጅ ለማስገባት የምናወጣውን ወጪ ለሌላ ልማት ማዋል ያስችለናል" ብለዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ ቢዝነስ መስሪያ መንገዶችን ከማቃለል ባለፈ ተወዳዳሪነትን በማጉላት የሕዝቡን ማህበረ-ምጣኔ ኃብታዊ ሁኔታ ማሻሻል ያስችላልም ነው ያሉት።

ኃይልን ማበልፀግ ቀጣናዊ ምጣኔ ኃብታዊ ውህደትን ለማፋጠን ያለውን ጠቀሜታ መረዳትና መረባረብ አስፈላጊ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

የጉባዔው ሊቀመንበርና የኬንያ የኢነርጂና ፔትሮሊየም ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ኃላፊ ዶክተር ፍሬድሪክ ኛንግ በበኩላቸው ኃይል ማልማት ብቻ ሳይሆን ድንበር ተሻጋሪ በሆነ መልኩ መጠቀምም ይገባል ይላሉ።

በምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ /ኮሜሳ/ አባል አገራት ኃይል የማመንጨት አቅም እ.አ.አ 2016 ከነበረበት 65 ሺህ ሜጋ ዋት በ2020 ወደ 92 ሺህ ሜጋ ዋት ማደጉንም ገልጸዋል።

እንዲያም ሆኖ የኃይል ማምረት ሂደቱ ከፀሃይ፣ ከንፋስ፣ ከጂኦተርማልና ከባዮ-ኢነርጂ ከመሳሰሉ የታዳሽ ኃይል ምርቶች ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ መክረዋል።

የተመረተውን ኃይል በቁጠባ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶክተር ፍሬድሪክ ዘርፉን በሕግና ስርዓት ማስተዳደር ይገባልም ብለዋል።

የኮሜሳ ረዳት ጻሃፊ አምባሳደር ኪፕዬጎ ቹሌጌት በበኩላቸው በቀጣናው ንግድና የፋይናንስ ልማትን እንዲሁም የኢንሹራንስ ስራዎችን ለማቀላጠፍ ኃይል ትልቅ ድርሻ አለው ይላሉ።

ከዚህ ጎን ለጎን ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና አስፈላጊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለማከናወን ኃይል ግድ የሆነበት ጊዜ መሆኑንም አብራርተዋል።

በመሆኑም የቀጣናው አገራት ተቀራርበው በመስራት ችግሩን ማቃለል እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

21 አገራትን በአባልነት የያዘው የኃይል ተቆጣጣሪዎች ማኅበር በኮሜሳ አስተባባሪነት ዘርፉን የማሳደግ ስራ እንደሚሰራም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም