ካራማራ እንደ አድዋ በብሔራዊ በዓልነት ሊከበር የሚገባው የኢትዮጵያውያን የጋራ የድል ታሪክ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26/2012(ኢዜአ) ካራማራ እንደ አድዋ የኢትዮጵያውያን የጋራ የድል ታሪክ በመሆኑ በብሔራዊ በዓልነት ሊከበር እንደሚገባው አንድ የታሪክ ምሁር ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በዚያድ ባሬ የሚመራውን የሶማሊያ እብሪተኛ ጦር ወረራ ድል የነሳችበት የካራማራ ድል ዛሬ 42 ዓመት ሞልቶታል።

በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች ቅርጫ ስር የነበረችው ሶማሊያ በ1952 ነጻ የወጡትን የጣሊያን ሶማሊላንድና የብሪቲሽ ሶማሊላንድን በማዋሃድ የሶማሊያን ሪፐብሊክ መሠረተች።

አዲሱ መንግስትም የኢትዮጵያ፣ ኬንያና ጅቡቲ ግዛቶች በመቁረስ ታላቋን ሶማሊያ ለመመስረት በማለም ትንኮሳ የጀመረው በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው የ1953 መፈንቀለ መንግስት ወቅት ነበር።

ሐረርጌን፣ ባሌን፣ አርሲን፣ ሲዳማንና ከፊል ሸዋን ያጠቃለለ አዲስ ካርታ በማዘጋጅት ድህረ ነጻነትን ተከትሎ በነበሩ 10 ዓመታት ስልጠና በመስጠት ታላቋን ሶማሊያ ለመገንባት እየጣረ ነበር።

በዚህም ኢትዮጵያ በአዲስ አብዮት በተጣደችበት ወቅት ዘመን በዚያድ ባሬ የሚመራው የሶማሊያ ጦር ሐምሌ 3 ቀን 1969 ዓ.ም ላይ ኢትዮጵያ አለመዘጋጀቷን በማየት በአካባቢው የነበረውን 3ኛ ክፍለ ጦርን ማጥቃት ጀመረ።

የወገን ጦር ባለው አቅም መከላከል ቢያደርግም በከፍተኛ የኃይል አለመመጣን ሳቢያ ወደኋል በማፈግፈጉ የጠላት ጦር ገላዲን፣ ቀብሪደሃር፣ ደጋሀቡር፣ ጎዴ፣ ሙስታሂል፣ ደወሌና ሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶችን በማለፍ በስተምስራቅ 700 ኪ.ሜ፣ በስተደቡብ 300 ኪ.ሜ. የኢትዮጵያን ሉአላዊ ግዛት ዘልቆ በኃይል ተቆጣጠረ።

እጅግ ዘመናዊና አይነት ብዙ የሶቪየት ሕብረትን ጦር መሳሪያዎች የታጠቀው የዚያድ ባሬ ጦር ጅጅጋን ከመቆጣጠር አልፎ ሀረር ከተማን በመክበብ በመድፍ ሲደበድብ ድሬዳዋን ለመቆጣጠር ቀረበ።

አሜሪካ ፊቷን ያዞረችባትና ትልቅ አደጋ ላይ የወደቀችው ኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ለማግኘት ወደ ምስራቁ የሶሻሊስት ጎራ ካሰለፈች በኋል ወታደራዊ ድጋፍ ማግኘት ጀመረች።

ለአብነትም ኩባ፣ ደቡብ የመንና ምስራቅ ጀርመን ለኢትዮጵያ የወገኑ ሲሆን በተለይም የፊደል ካስትሮ ኩባ ከ18 ሺህ በላይ እግረኛና ሜካናይዝድ ጦር ድጋፍ በማድረግ መስተዋትነት ከፍላለች።

በቂ የመሳሪያና ሰራዊት ያልነበረው የእናት አገር ጥሪ በማወጅ በቂ የስልጠና ግብዓት ባልነበረው የታጠቅ ማሰልጠኛ ጣቢያ ላይ ከ300 ሺህ በላይ ሰራዊት በማሰልጠን እንደ አድዋው ዘመን ዘመቻ ክተት ተባለ።

ከሐምሌ 1969 ዓ.ም እስከ የካቲት 1970 በጀግንነት ሲዋጋ የቆየው የኢትዮጵያ ጦር የዛሬ 42 ዓመት የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም ጅግጅጋ በስተሰሜን ምዕራብ ከሚገኘው የካራማራ ተራራ ጠላትን ድል አድርጎ ሰንደቅ ዓላማውን አውለበለበ፤ የጠላት ጦርም ስንቁን እየጣለ ሽንፈቱን ተጎንጭቶ ኢትዮጵያን ለቆ ወጣ።

በኢትዮ-ሶማሌያ ወይም የኦጋዴኑ ጦርነት ከኢትዮጵያ ወገን 18 ሺህ ሰዎች የሕይወት መስዋትነት ሲከፍሉ 29 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ቆስለዋል፤ 450 የሚሆኑት ተማርከዋል።

የክፉ ቀን አጋር የሆነችው ኩባ 163 እና የመን 100 ወታደሮች ሲሞቱ፤ ከሶማሊያ ወገን ከ15 ሺህ 900 በላይ ሲሞቱ 26 ሺህ በላይ ቆስለዋል፣ ከ1 ሺህ 700 በላይ ተማርከዋል።

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራመሪው ዶክተር ቴዎድሮስ ሃይለማርያም ''ካራማራ በአድዋ ላይ የነበሩ ብሔራዊ ነጻነት፣ የአገር ፍቅርና ጀግንነት የታየበት የድል ቀን ነው'' ባይ ናቸው።

''ዳሩ ግን ከደርግ ስርዓት መወደቅ በኋላ ባለው የዘመናዊ ፖለቲካ ተቃርኖ የዘውግ ፖለቲካ የጋራ ታሪክ እሴት በማሳጣት ይህ አኩሪ ብሔራዊ ድል ቀን እንዲዘነጋ አድርጓል'' ብለዋል።

ከየአገሩ በአጭር ጊዜ ተሰባስቦ ድል ያመጣው የ'ገበሬ' ሰራዊት ድል መዘንጋቱ እንዳሳዘናቸው ይገልጻሉ።

የኦጋዴኑ ጦርነት የድህረ ቅኝ ግዛት ዘመን በአፍሪካ ትልቁ ጦርነት እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ቴዎድሮስ፤ በአድዋ ላይ ጎልቶ የታየው የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ጀግንነት የተደገመበት መሆኑን ተናግረዋል።

በቁጥር አነስተኛ ቢሆንም የኢትዮጵያ አየር ሃይል አባላት አኩሪ ጀብዱ የፈጸሙበት፣ በአድዋው ከተሰዋው ሰራዊት ሶስት እጥፍ የሚጠጋ ሰራዊት ያለቀበት ጦርነት መዘንጋት እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

በመሆኑም የካራማራ ድል እንደ አድዋ በብሔራዊ በዓልነት መከበር እንዳለበት ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም