በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላምና ፍቅርን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ የኃይማኖት አባቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላምና ፍቅርን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ የኃይማኖት አባቶች ገለጹ
መቀሌ ሰኔ 21/2010 በኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል ለዓመታት የቆየውን ዝምታ በመስበር ሰላምና ፍቅርን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ በትግራይ ክልል አስተያየታቸውን የሰጡ የኃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡ ጥረቱን ከዳር ለማድረስ የዘወትር የስራቸው አካል እንደሚያደርጉም አመልክተዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኃይማኖት አባት መልአከ ህይወት ግደይ ሓዱሽ እንዳሉት፣ሰላምን ለማረጋገጥ በሁለቱ ሀገራት መንግስታት መካከል የተጀመረው ጥረት ዘላቂ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም በድንበር አካባቢ ያሉትን የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች በዋነኛነት ማሳተፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የእስልምና የሃይማኖት አባት የሆኑት ሐጂ መሓመድ ካሕሳይ በበኩላቸው፣ የኃይማኖት ተቋማቱ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ሰላምና ፍቅር እንዲሰጥ የመጀመሪያ ትኩረታቸው አድርገው የሚያስተምሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላምና ፍቅርን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ወደ ታች ወርዶ እንዲሳካ የሚደግፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በሁለቱም ህዝቦች መካከል ለዘመናት የነበረው ፍቅርና አንድነትን ይበልጥ የሚጎለብተው በድንበር ምክንያት በሁለቱም መንግስታት ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ሲፈታ ነው " ያሉት ደግሞ የኢትዮጰያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የኃይማኖት አባት አባ ጥዑም በርሄ ናቸው፡፡ እንደ ኃይማኖት አባትነታቸው ለዘላቂ መፍትሄው ቅድሚያ በመስጠት የነበረውን ችግር ለመፍታት የተጀመረውን ጥረት እንደሚደግፉ ተናግረዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ላመጡት ለውጥ ምስጋና ለማቅረብ በአዲስ አበባ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ወቅት በንጹሃን ዜጎች ላይ በደረሰው የሞትና የአካል ጉዳት የኃይማኖት አባቶቹ የተሰማቸውን ሃዘን በመግለጽ ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡ የኃይማኖት አባቶቹ እንዳሉት፣ጠቅላይ ሚኒስተሩ በሀገሪቱ ሰላምና ፍቅር እንዲመጣ እያሳዩት ያለውን ጥረት በህዝቦች መካከል ይበልጥ መቀራረብን የሚያመጣ ነው። ሆኖም ሰልፉን ተከትሎ የህዝቦችና የኃይማኖቶች እኩልነት ምልክት ከሆነው ሰንደቅ ዓላማ ጋር የሚፃረር ህጋዊ ያልሆነ ተግባር መታየቱ ተገቢ እንዳልሆነ የካቶሊክ ኃይማኖት አባት የሆኑት አባ ጥዑም በርሄ ተናግረዋል፡፡ በሰላማዊያንና ንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመው እኩይ ተግባር በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት እንደሌለው የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተከርስቲያን የኃይማኖት አባት ምሕረተአብ ብርሃነ ናቸው፡፡ የመደመር ፕሮግራሙ ህዝቦች የሚያቀራርብ፣ አንድነትና ፍቅርን የሚያጠናክር በመሆኑ እንደሚደግፉት ተናግረዋል።