ቀጥታ፡

ግድቡ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል -የነገሌ ነዋሪዎች

ነገሌ፣ የካቲት 26/ 2012 ዓ.ም(ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት እስኪበቃ ድረስ ማንኛውንም ጫናና ተፅእኖ በመቋቋም ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ 


ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የጉጂ ዞን ሸሪአ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ከድር አብዱረህማን እንደገለፁት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ወዲህ አቅማቸውን የፈቀደው በማዋጣትና ቦንድ በመግዛት የድርሻቸውን ሲያበረክቱ ቆይተዋል።

አሁንም በክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተደረገውን ጥሪ በመቀበል ግድቡን እንደጀመርነው ለመጨረስ አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የግድቡን ግንባታ በማደናቀፍ የተፈጥሮ ሀብታችንን የመጠቀም መብት ለመንፈግ በአንዳንድ የውጭ ሃይሎች እየተፈጠረ ያለውን ጫናና ተፅእኖ ተገቢነት የለውም ያሉት  ሼህ ከድር በእልህና በወኔ ግንባታውን ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በሙሉ አቅማችን እንረባረባለን ብለዋል ።

በሀገር ውስጥ አለመግባባት ቢኖርም መብቶቻችንና ጥቅሞቻችንን ለማስከበር አንድ ሆነን በመነሳት ጠላትን መክቶና አሳፍሮ የመመለስ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች እንዳሉን ማንም ሊገነዘበው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የነገሌ ከተማ ነዋሪ መምህር መብራቱ ባህሩ በበኩላቸው በእውቀትና በስነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ከማፍራት ጎን ለጎን በልማቱ መስክም አርአያ ሆነው ለማገልገል ፅኑ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል ።

ከአሁን በፊት በሁለት ዙር ቦንድ መግዛታቸውን የገለፁት መምህር መብራህቱ አሁንም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ርብርብ አሻራቸውን ለማሳረፍ ተሳትፎአቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ተናግረዋል ።

ከጉጂ ዞን ፖሊስ በጡረታ የተገለሉት ኮማንደር ነገሪ ጂማ እንዳሉት ደግሞ የህዳሴ ግድብ በገንዘብና በጉልበት ከማገዝ ባለፈ የህይወት መስዋእትነት ቢጠይቅም ተገቢውን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ከፖሊስ ሰራዊት አባልነት በጡረታ ከመገለላቸው በፊት ሶስት ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀው፤ አሁንም ሆነ ለወደፊቱ አገራዊ ጥሪውን በመቀበል የሚፈለግባቸውን ድጋፍ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል ።

የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ባለፉት ሁለት አመታት ተቀዛቅዞ መቆየቱ ይቆጫቸው እንደነበር የተናገሩት ኮማንደሩ የተፈጥሮ ሀብታችንን የመጠቀም መብት እንዳለን በተግባር ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ ለመሳተፍ የሚያቅማማ ህዝብ እንደማይኖር እምነታቸውን ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም