ቀጥታ፡

የባዮ ቴክኖሎጂ አንስቲትዩት የዶሮ ኮሌራ መድሃኒትን አገኘ

የካቲት 26/2012 ዓ.ም (ኢዜአ ) የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ አንስቲትዩት የዶሮ ኮሌራ መድሃኒትን ሰርቶ ወደ አፍሪካ ገበያ እንዲገባ ማድረጉን አስታወቀ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ የመስሪያ ቤቱን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ኢንስቲትዩቱ የዶሮ ኮሌራ መከላከያ ክትባት ምርምርን በመደገፍ መድሃኒቱ ወደ ገበያ እንዲገባ ማድረጉንና የዶሮ ፈንግል በሽታን ለመከላከል የሚያስችል ምርምርም በማድረግ ተስፋ ሰጪ ውጤት እያሳየ መሆኑም ተገልጿል።

በግለሰብ ደረጃ የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ የሚታሰበው ከጥንቅሽ ጭማቂን ለማምረት የሚያስችል የመጭመቂያ ማሽን በሀገር ውስጥ በብዛት እየተመረተ መሆኑንና በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋየ ተናግረዋል።

የወባ ማባረሪያ መድሃኒት፣ ውሃ ጠል ቁስ፣ ከሸንኮራ ውጋጅ ከአካባቢ ብክለት የፀዳ ከሰል ማምረት፣ አፍላ ቶክሲንን መከላከል ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችም ውጤት የተመዘገበባቸው ስራዎች ናቸው።

የቡና ገለፈትን በትሎች በማስበላት ወደ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ የሚቀይረው ፕሮጀክትም ተጠናቆ ወደ ስራ መግባቱ ተብራርቷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ተቋሙ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ምርምሮች ወደ ገበያ መውጣት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ላይ በትኩረት እንዲሰራ ከሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም