ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል ቁፋሯቸው የተጠናቀቁ ሶስት የተፈጥሮ ጋዝ ማመንጫ ጉድጓዶች የሙከራ ምርት ጀመሩ

ጅግጅጋ ሰኔ 21/2010 በቻይናው ፖሊ ጂሲኤል ፔትሮሊየም ሆልዲንግ የተባለው ኩባንያ በምስራቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በቁፋሮ ላይ ካሉ የተፈጥሮ ጋዝ ማመንጫ ጉድጓዶች መካከል ሶስቱ ተጠናቆ ድፍድፍ ነዳጅ የሙከራ ምርት ዛሬ ጀመሩ፡፡ የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ መለስ አለሙና የክልሉ ርስሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሐመድ የሙከራ ምርት የጀመሩትን ጉድጓዶቹን  መርቀዋል፡፡ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ኢንጀነር እድሪስ ኢስማኤል ለኢዜአ በስልክ እንደገለጹት የሙከራ ነዳጅ ማውጣት ሰራቸውን የጀመሩት በጎዴ ዞን ኢላላ ወረዳና ቆራሃይ ዞን ሽላቦ ወረዳዎች ቁፋሯቸው የተጠናቀቁ ሶስት ጉድጓዶች ናቸው ። ጉድጓዶቹ የሙከራ ምርት ስራቸውን በይፋ መጀመራቸው የክልሉ ህዝብ ለሰላም የከፈለው የመስዋእትነት ፍሬ ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምስራቅ ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየው  የነዳጅ ፍለጋ ስኬታማ በመሆኑ ከዛሬ  ጀምሮ ኢትዮጵያ ድፍድፍ ነዳጅ የማምረት ሙከራ እንደምትጀምር ፤  ከመጪው መስከረም አንስቶ በሁለት ዓመታት ውስጥ የሚጠናቀቅ  የነዳጅ ቱቦ ዝርጋታ ወደ ጂቡቲ እንደሚካሄድ  ትናንት ይፋ ማድረጋቸውን በወቅቱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም