ቀጥታ፡

የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት በኢትዮጵያ ለአንበጣ መከላከያ የ4 ነጥብ 5 ሚሊዬን ዶላር ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገባ

 አዲስ አበባ የካቲት 25/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል የዓለም የእርሻና የምግብ ድርጅት የ4 ነጥብ 5 ሚሊዬን ዶላር ድጋፍ ለማድርግ ቃል ገብቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ለአንበጣ መንጋ መከላከያ የሚውል 30 ሚሊዬን ብር መድቧል። 

በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ መጠን በየወቅቱ እየጨመረ በመምጣቱ በዜጎች የምግብ ዋስትና ላይ አደጋ ደቅኗል።

ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በአማካይ አንዱ መንጋ ከ40 አስከ 80 ሚሊዮን የያዘ እስከ ሶስት የአንበጣ መንጋ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ቀጥሏል።

የመንን ጨምሮ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያና ሌሎችም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በቅንጅት መከላከል ባለመቻላቸው ስርጭቱን ለመቆጣጠር እንቅፋት መሆኑም እየተነገረ ነው።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ከባለፈው ሰኔ ጀምሮ በሁለት ዙር የባህላዊ መንገድና የኬሚካል ርጭት በመጠቀም ስርጭቱን 90 በመቶ መቀነስ ተችሏል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ቦታዎች በመኪና እና አውሮፕላን ለመርጨት አስቸጋሪ በመሆኑ፤ በባህላዊ መንገድ ለማስወገድ ሲባል ስለሚበታተኑ የቁጥጥር ሂደቱን ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል።  

በቅርቡ አማራ ክልል ጎጃም አካባቢ የተከሰተውም በንፋስ ሃይል ምክንያት ከኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ - በኩል የተዛመተ መሆኑን ገልጸዋል።

የአንበጣ መንጋ ከመካከለኛው ምስራቅ በየመን - ሶማሊያ አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው በሶማሌ፣ አፋር፣ ምስራቅ አማራ፣ ደቡብ ትግራይ አካባቢዎችን እንደሚያጠቃልል ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የነፋሱ አቅጣጫ በመቀየሩ ከሳውዲ አረቢያና ፓኪስታን በመነሳት በደቡባዊ ሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በመዛመት ወደ ኬንያ ይሻገራል ብለዋል።

የአንበጣ መንጋው ከተበተነ በኋላ የት እንደተሰበሰብ ለማወቅ ፈታኝ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በድሮን የታገዘ የመረጃ አሰባሰብ ስልት ለመጠቀም ከቻይና መንግስት ድጋፍ ለማግኘት እየተነጋገሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ከመካከለኛው ምስራቅ የሚመጣው የበረሃ አንበጣ መንጋ ኢትዮጵያ እስከሚገባ ከተፈለፈለ 50 ቀናት ስለሚሆነው በእርጥበታማ ቦታዎች እንቁላል እየጣለ ይራባል፤ አንድ አንበጣ ደግሞ በየሳምንቱ እስከ 120 ሺህ እንቁላል የመጣል አቀም እንዳለው ገልጸዋል።

በምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ እስከ መጭው ነሐሴ ወር ሊቆይ እንደሚችል ትንበያ አለ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኢትዮጵያም ይሄን ታሳቢ በማድረግ በባህላዊ መንገድና በአውሮፕላን ርጭት ለመከላከል ተዘጋጅታለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ለዚህ ዓላማ 30 ሚሊዬን ብር መድቦ እየተንቀሳወቀሰ ሲሆን፤ የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት 4 ነጥብ 5 ሚሊዬን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱን ገልጸዋል።

የበረሃ አንበጣን ለመከላከል የመንግስት ብቻ ሃላፊነት አለመሆኑን ገልፀው ኅብረተሰቡም በባህላዊ መንገድ በመከላከል የሚናውን ማጠናከር አለበት ብለዋል።

 ኅብረተሰቡም የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል የሚረጨው ኬሚካል "በእንስሳትና ሰው ላይ ጉዳት ያደርሳል" በሚል በሚሰራጨው የተሳሳተ መረጃ መደናገር እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ ለቀጠናው ስጋት በመሆኑ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር በጋራ ለመከላከል በቅንጅት ትስራለችን ብለዋል።

የበረሃ አንበጣ እስከ 90 ቀን እደሜ ያለው ሲሆን ከ50ኛ ቀኑ በኋላ የመራባት አንጂ በሰብል ላይ ጉዳት የማድረስ አቅሙ ውስን መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም