ቀጥታ፡

ፍትሃዊ ምርጫ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ታማኝነትና ገለልተኝነትን ይጠይቃል

 አዲስ አበባ የካቲት 25/2012 (ኢዜአ) ሀገራዊ ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሒደቱን በታማኝነትና በገለልተኝነት መዘገብ እንዳለባቸው ተጠየቀ።

የአሜሪካ ኤምባሲ ከጆንስ ሆፕኪንስ የኮሚኒኬሽን ማዕከል ጋር በመተባበር በምርጫ አዘጋገብ ላይ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ፤ በቅድመና ድህረ- ምርጫ ወቅት የመገናኛ ብዙሃን የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የባለሙያዎችን አቅም በመገንባት ረገድ ተከታታይ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ተቋማቱ የምርጫ ሂደቱን ከመዘገብ ባለፈ የመራጩን ህዝብ ግንዛቤ ማሳደግ አለባቸው ያሉት አማካሪዋ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አጀንዳ ከማስተዋወቅ አኳያም ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በአሁን ጊዜ በአገሪቷ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ተዋናዩቹን አቅም በመገንባት ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡም ተከታታይ ስልጠና ማስፈለጉንም ተናግረዋል።

ቦርዱ ለተቋማቱ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ያሉ መረጃዎችን በፍጥነት ከማድረስ አኳያ የሚፈለገውን ያህል ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ያደርጋልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዷለም፤ ባለስልጣኑ መገናኛ ብዙሃን ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ትዕዛዝ ከማስተላለፉ በፊት የራሱን አቅም መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙሃኑ የተጣለባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ በባለሙያዎች ሊመሩ የሚገባ ሲሆን ለዚህም ባለስልጣኑ የአቅም ግንባታ ስራዎችን እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ጋዜጠኞች መጪው ብሄራዊ ምርጫ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ከወገንተኝነት ነጻ ሆነው ለመራጩ ህዝብ ትክክለኛ መረጃ እንዲያስተላልፉም ጠይቀዋል።

የሆርን ኦፍ አፍሪካ የደህነነት ጥናት ተቋም ተመራማሪ ዶክተር ሰሚር የሱፍ በበኩላቸው የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሽግግር እውን አንዲሆን በቁርጠኝነት እገዛ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

መንግስታትን ከተቃርኖ ፖለቲካ ማውጣትና የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ማስገንዘብም የተቋማቱ ዋነኛ ስራ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

ተቋማቱ ቀጣዩን ምርጫ በተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ባለፈ የህዝቡን ስሜት በትክክል ማስተናገድ እንዳለባቸውም ዶክተር የሱፍ ተናግረዋል።

ስድስተኛው ብሄራዊ ምርጫ ነሃሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም