በደቡብ ክልል ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው
ሀዋሳ የካቲት 25/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በመቅጣትና ቤተሰብ ተኮር የማህበረሰብ ውይይት በማመቻቸት ድርጊቱን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉሰው ዘውዴ ለኢዜአ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 74 ግለሰቦች በህግ ወጥ አዘዋዋሪነት ፍርድ ቤት ተከሰው ከአምስት እስከ 25 ዓመት የእስራት ቅጣት ተልፎባቸዋል።
እንዲሁም በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ 42 መዝገብ ተደራጅቶ ከዚህ ውስጥ በ38ቱ ክስ መመስረቱን አመልክተው ከነዚህ ውስጥ 18 መዝገቦች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ መተላለፉን አስታውቀዋል።
"ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው በመሆኑ በዜጎች ላይ ሰብአዊ የመብት ጥሰት እያደረሰ ያለው አደጋ የከፋ ነው "ብለዋል፡፡
በክልሉ እየተስፋፋ የመጣውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደትን ለመከላከል ተጋላጭ አካባቢዎችን ማዕከል በማድረግ ግንዛቤ ከመፍጠር በተጓዳኝ ልዩ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ህግ ለማስከበር ጥረት እየተደረገ ነው።
በክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሥራ ሥምሪት አገልግሎት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ በዛብህ በበኩላቸው በክልሉ ከ900 በላይ ቀበሌዎች ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የስደት አስከፊነት የሚያሳዩ አጀንዳዎች ተመርጠው ቤተሰብ ተኮር የማህበረሰብ ውይይት በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከ300 በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ደግሞ የአቻ ለአቻ የህይወት ክህሎት ውይይትና ስልጠና እየተሰጠ ነው።
እንደ አቶ ታሪኩ ገለጻ ዜጎች ህገ ወጥ ጉዞን ምርጫ እንዳያደርጉ ከሆነም በመረጃ ተደግፈውና ሙያዊ ክህሎት ኖሯቸው እንዲንቀሳቃሱ ለማመቻቸት በተደረገው ጥረት ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ8 ሺህ በላይ ሰዎች ስልጠና ወስደዋል።
ሆኖም ከውጭ ሃገራት ጋር የሚፈጠረው የስራ ስምሪት አፈጻጸም መጓተት ከፈላጊው ቁጥር ጋር አለመመጣጠኑ ለደላሎች እንዲጋለጡ እያደረገ በመሆኑ ሊሰራበት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
በህገ-ወጥ ደላሎች ተታልለው በመሄድ ለጉዳት ተዳርገው ወደ ሀገር የተመለሱ ዜጎችን ለማቋቋም በመንግስት ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በህገ-ወጥ መንገድ ሳዐዲ በመሄድ ለከባድ ጉዳት ተጋልጣ ባዶ እጇን መመለሷን የተናገረች ደግሞ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሪት ተዋበች ባዩ ናት።
ወደ ሀገር ቤት ከተመለሰች በኋላ መንግስት የሥራ ቦታ ሰጥቶ ተስፋዋን እንዳለመለመው ገልጻለች።
ወጣት ጸጋ ገብረጻድቅ በበኩሏ በስደት በሄደችበት ዓረብ ሃገር ከፍተኛ የጤና መታወክ ገጥሟት መመለሷን አስታውሳ መንግስት ሙሉ ወጪዋን ሸፍኖ አስክሟት ጤናዋ ተመልሶ መንቀሳቀስ እንደቻለች ትናገራልች፡፡
"የራሴን የገቢ ምንጭ እንድፈጥር መንግስት የሥራ ቦታ በመስጠት ድጋፍ አድርጎልኛል " ብላለች።
ወላይታ፣ሃዲያ፣ጉራጌ፣ ስልጤ፣ጋሞ፣ ሃላባ፣ ጎፋ፣ ከምባታና ጣምባሮ ዞኖች ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጋላጭ ከሆኑት የክልሉ አካባቢዎች መካከል ይገኙበታል።