አዳዲስ የግብር አሰባሰብ መመሪያዎች ለባለሙያዎች ግንዛቤ እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዳዲስ የግብር አሰባሰብ መመሪያዎች ለባለሙያዎች ግንዛቤ እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ የካቲት 25/2012 (ኢዜአ) ለግብር አሰባሰብ ስርአቱ የወጡ አዳዲስ መመሪያዎች ደንበኞችን ለእንግልት እንዳይዳርጉ ለዘረፉ ባለሙያዎች ግንዛቤ መሰጠቱ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለስልጣን በመመሪያ፣ አሰራር፣ ማኑዋልና በአገልግሎት ጽንሰ ሃሳብ ላይ ከሁሉም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ለተውጣጡ ቡድን አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው።
ስልጠናው ሙያተኞች በመመሪያዎች ላይ ግልጽ ግንዛቤ ኖሯቸው ለደንበኞች በእውቀት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።
በባለስልጣኑ የደንበኞች መስተንግዶና ድጋፍ ዳሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዘውዴ የግብር አሰባሰብ ስርአቱን አስመልክቶ የወጡ አዋጅና መመሪያዎች ላይ በአገልግሎት ሰጪዎች ዘንድ የጠራ ግንዛቤ ባለመኖሩ ግብር ከፋዮች የሚንገላቱበት ሁኔታ መኖሩን አንስተዋል።
"ስልጠናው ግብር ከፋዩ ወደ ታክስ መረቡ ሲገባና ሲወጣ ህግና መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ ቀላልና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ ያግዛል" ብለዋል።
አገልግሎት ሰጪዎች የግብር ከፋዮችን መብትና ግዴታ በግልጽ በማስረዳት ተገልጋዮችን ለእንግልት የሚዳርጉ አሰራሮችን እንዲያስቀሩ የሚያግዝ መሆኑን ዳይሬክተሯ አመልክተዋል።
"ይህም ደንበኞችን በእውቀት ላይ ተመስርተው በማስተናገድ ሊደርስባቸው የሚችለው እንግልት እንዲቀንስ ያደርጋል" ብለዋል።
ለደንበኞች ቀልጣፋና በዘመናዊ አሰራር የተደገፈ አሰራርን ለማጠናከር የአገልግሎት አሰጣጥ ጽንሰ ሃሳብ በስልጠናው ላይ እንዲካተት ተደርጓል።
በግብር ከፋዮች በኩል የሚስተዋሉ ግብርን በወቅቱ አለማሳወቅ፣ ግብር መሰወርና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት መረጃ የማጠናከር ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ አቻም ጨመረ እንደሚሉት ስልጠናው ለደንበኞች በእውቀት ላይ የተመሰረተና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ ነው።
በመመሪያዎችና ደንቦች ላይ እየተሰጠ ያለው ስልጠና ቀደም ሲል ከደንበኞች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የነበረባቸውን ችግር እንደሚቀንስ የተናገሩት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ኃይሉ በዳዳ ናቸው።
በሁለት ዙር የሚሰጠው ስልጠናው ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል።
ባለስልጣኑ ባለፉት ሰባት ወራት 25 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 24 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል።
ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ጭማሪ እንዳለው ተገልጿል።
በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ ያቀደውን 37 ቢሊዮን ብር ለማሳካትም በቀሪዎቹ ወራት በትኩረት እንደሚሰራ ተነግሯል።
በአዲስ አበባ ከ344 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች የሚገኙ ሲሆን 15 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችና 6 የታክስ ማዕከሎች ይገኛሉ።