ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔና የውሳኔ ግልባጭ በአንድ ላይ መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔና የውሳኔ ግልባጭ በአንድ ላይ መስጠት ጀመረ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 25/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 1ኛ ሰበር ችሎት ውሳኔ በሰጠበት ቅጽበት ባለጉዳዩ የውሳኔውን ግልባጭ ማግኘት የሚችልበትን አሰራር ተግባራዊ አደረገ።
በየወሩ የመጨረሻ ሳምንት የሚሰጠውን ውሳኔ በግልጽ ችሎት ሲያሳውቅ የቆየው ችሎቱ ከየካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የውሳኔ ግልባጩን ውሳኔውን በገለጸበት ችሎት ለባለጉዳዮች መስጠት መጀመሩን የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ ዶክተር ተፈሪ ገብሩ ገልጸዋል።
አሰራሩ ባለጉዳዮች ውሳኔ ካገኙ በኋላ የውሳኔ ግልባጭ ለማግኘት በርካታ ቀናት ሲወስድባቸውና ወደ ፍርድ ቤቱ መዝገብ ቤት ከሶስት ጊዜ በላይ እንዲመላለሱ የሚያደርገውን አሰራር በማስቀረት ከእንግልት ያዳነ ነው ተብሏል።
የሰበር ችሎቱ የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት ለ17 መዛግብት ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ለሁሉም ባለጉዳዮች የውሳኔ ግልባጭ ወዲያው በመስጠት ስራውን ጀምሯል።
ይህ አሰራር የዳኝነት አገልግሎቱን ቀልጣፋነት ለማሻሻል ለሌሎች ችሎቶች ማሳያ የሚሆን ተግባር እንደሆነም ተገልጿል።
አሰራሩ ፍርድ ቤቱ ያጣውን የህዝብ አመኔታ ለመመለስ መልካም አጋጣሚ እንደሆነለትና ያልተገቡ ብልሹ ተግባራትን ለመቀነስ ዕድል እንደሚፈጥር የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ ጠቅሰዋል።
ባለ ጉዳዮች የውሳኔ ግልባጩን እንዳገኙ የአገልግሎት ክፍያ የሚፈጽሙበትና ሰነዱን ህጋዊ የሚያደርጉ ሂደቶችን ከችሎቱ አቅራቢያ በተደራጀ የሰው ኃይል በ10 ደቂቃ እንዲያገኙም ተደርጓል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን እጅጉ በበኩላቸው ችሎቱ በጀመረው አዲስ አሰራር የተስተዋሉ ጥቃቅን ጉድለቶችን በማረም ስራውን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።