ቀጥታ፡

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንደግፋለን- ተፎካካሪ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ ሰኔ 21/2010 በኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል ሰላም ለመፍጠር እየተደረገ ባለው መልካም ጅምር የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በሁለቱ አገሮች መካከል ለዓመታት ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እልባት እንዲያገኝና ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳኢያስ አፈወርቂ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር የሀገሪቱን ከፍተኛ የመንግሥት ልዑክ ወደ አዲስ አበባ ልከዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላም ለመፍጠር በተጀመረው ጥረት በኢትዮጵያ ያሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል። የቅንጅት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ የህግ ክፍል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ዎይሻ የሁለቱ ሀገራት ጉዳይ በሰላምና በፍቅር እንዲፈታ የፓርቲው ፍላጎት እንደነበር ገልጸው ከኤርትራ ጋር የሚኖረው ሰላማዊ ግንኙነት “የውስጣችንንም ሰላም ያጠናክራል” ብለዋል፡፡ ፓርቲያቸው ለዓመታት የቆየውን ችግር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ከመንግሥት ጎን ሆኖ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበሩ አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው ከኤርትራ ጋር ሰላም ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት  ብቻ ሳይሆን በሁሉም ረገድ  የተጀማመሩ ነገሮች ተስፋ የሚሰጡ በመሆናቸው ሁሉም ሰው በሃላፊነት መንፈስ እንዲንቀሳቀስ ጠይቀዋል፡፡ የመላ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ)  ዋና ጸሃፊ አቶ ዘመኑ ሞላም  በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው የድንበር ውዝግብ “አንድ እልባት ያመጣል” የሚል ተስፋ መሰነቃቸውን ገልጸው የተጀመረው ውይይት ለፍሬ እንዲበቃ ፓርቲያቸው የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልካም ስራዎች ለማበረታታት እየተደረጉ ያሉ የድጋፍ ሰልፎች  በቀጣይ ለሚያከናውኗቸው ተግባራት የሞራል ስንቅ እንደሚሆኗቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያከናውኗቸውን  የለውጥ ተግባራት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በሚሊዮን የሚቆጠር የአዲስ አበባና አካባቢዋ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ድጋፉን መግለጹ የሚታወስ ነው። በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች  የድጋፍ ሰልፉ ቀጥሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም