ቀጥታ፡

የሞጆ-ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ የመጀመሪያ ምዕራፍ ከአምስት ወራት በኋላ ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ የካቲት 25 /2012 (ኢዜአ) የሞጆ-ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሆነው የሞጆ-መቂ 56 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር መንገድ ከአምስት ወራት በኋላ ይጠናቀቃል ተባለ። 

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የፍጥነት መንገዱ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እያስጎበኘ ነው።

በ13 ነጥብ 58 ቢሊዮን ብር የሚገነባው የሞጆ-ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ 202 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።

ይህ መንገድ ከአዲስ አበባ-አዳማ የፍጥነት መንገድ ጋር የሚገናኝ ነው።

የመንገዱ ግንባታ በአራት ምዕራፎች ተከፍሎ እየተከናወነ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በ2008 ዓ.ም የተጀመረው የሞጆ-መቂ መንገድ በቀጣዮቹ አምስት ወራት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

የሞጆ-መቂ 56 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር መንገድ 88 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ግንባታውን የሚከውነው  የቻይናው ሬይል ዌይ ሰርቪስ ግሩፕ ነው።

37 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የምዕራፍ ሁለት የመቂ-ዝዋይ መንገድ ደግሞ 79 በመቶ የተናቀቀ ሲሆን ግንባታውን ዴይዋ ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን የተሰኘ የቻይና ኩባንያ እየሰራው ይገኛል።

የሞጆ-ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ የአካባቢውን የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችልም ነው።

የአዲስ አበባ፣ ሞያሌ፣ ናይሮቢና ሞምባሳ ያለውን የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ እንቅስቃሴ እንደሚያሳልጥም ተነግሯል።

የፍጥነት መንገዱ 10 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የምስራቅ አፍሪካ መተላለፊያ ኮሪደር ከካይሮ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬፕታውን የትራንስ-አፍሪካ ሀይዌይ አካል በመሆንም የአካባቢውን አገራት ኢኮኖሚ ያስተሳስራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም