ቀጥታ፡

የአፍሪካ አቪዬሽን ጠንክሮ እንዲወጣ የመንግስታትን ትኩረት ይፈልጋል

 አዲስ አበባ የካቲት 25/2012 (ኢዜአ)  ውስብስብ ችግሮች ያሉበት የአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ጠንክሮ እንዲወጣ የመንግስታት የቅርብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው የዘርፉ ተዋናዮች አሳሰቡ።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው አምስተኛው የአፍሪካ አቪዬሽን ጉባኤ "ለኢንዱስትሪው ቀጣይነት ያለው ሁኔታ መፍጠር" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም "የአፍሪካ አቪዬሽን መልካም አጋጣሚዎች ቢኖሩትም ችግሮቹም በዛው ልክ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።

ከችግሮቹ መካከልም የአገራት መሪዎች ለአየር መንገዶቻቸው ያላቸው ያልተገባ እይታ ዋነኛው መሆኑን ጠቁመዋል።

ዘርፉ ከሲጋራና ከአልኮል መጠጦች በላይ ከፍተኛ ታክስ የሚጣልበት መሆኑን በማሳያነት በመጥቀስ።

"ከአየር መንገዶች ግንባታ ጀምሮ የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዲሁም ከፍተኛ የመጓጓዣ ክፍያ ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያህል እንዳያድግ አድርጓል" ነው ያሉት።

የአውሮፕላን ነዳጅ ወጪም ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር ሲነጻጸር በአፍሪካ 30 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ የዘርፉ ሌላው ማነቆ መሆኑን ተናግረዋል።

በአህጉሪቷ አየር መንገዶች መካከል የሚታየው ያልተገባ ውድድርና የትብብር መንፈስ አለመኖር ትልቅ ችግር እንደሆነም አንስተዋል።

"የኢትዮጵያ አየር መንገድ እነዚህን ሁሉ ችግሮች ተቋቁሞ ከ70 ዓመታት በላይ አህጉሪቷን ከተቀረው ዓለም ጋር አገናኝቷል" ብለዋል አቶ ተወልደ።

በዚህም ለመገናኘት በአውሮፓ በኩል ይጠቀሙ የነበሩ እነ ቶጎ፣ ቻድ፣ ማላዊና ሞዛቢክን የመሳሰሉ የምዕራብና የመካከለኛው አፍሪካ አገራትን ማቀራረብ መቻሉን ነው የገለጹት።

እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱ ታዲያ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ዘርፉን በሁሉም መስክ በእኩል ዓይን መመልከትና ማገዝ ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።

የአቪዬሽን አፍሪካ ሊቀመንበር አለን ፒፎርድ "ከነበሩት ችግሮች በላይ ወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ዘርፉ ላይ ስጋት እንዲያንዣብብ አድርጓል" ይላሉ።

"የአፍሪካ ትላልቅ አየር መንገዶች ላይ እስከ 20 በመቶ የተጓዞች ፍላጎት መቀነስ ታይቶባቸዋል" ያሉት ሊቀመንበሩ ስጋቱ ሌሎችንም እንዳሳሰበ አመልክተዋል።

ሊቀመንበሩ በአፍሪካ አቪዬሽን ከፍተኛ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እንዲሁም የአየር ክልሎችን ከፍት አድርጎ መጠቀምን ተጨማሪ የዘርፉ ችግሮች እንደሆኑ ገልጸዋል።

የአፍሪካ አገራት የዘርፉን ችግሮች ለማቃለልተቀራርበው መስራት አለባቸው ያሉት ደግሞ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ናቸው።

ዘርፉ ይበልጥ ውጤታማ ይሆን ዘንድ የግሉን ዘርፍ በስፋት ማሳተፍና የግልና የመንግስትን አጋርነት መተግበር የተሻለ አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዘርፉን የመሰረተ ልማት ዝርጋታና እንቅስቃሴ ማዘመንም ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ መክረዋል።

ከጉባኤው ጎን ለጎን በአፍሪካ አቪዬሽን ዘርፍ የተሰማሩ የተለያዩ አካላት ምርትና አገልግሎቶቻቸውን ያቀረቡበት ኤግዚቢሽን ተከፍቷል።

በአፍሪካ 80 በመቶ የሚሆነው የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የሚመራው አፍሪካዊ ባልሆኑ አየር መንገዶች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ዘርፉ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ በዓመት እስከ 7 ቢሊዮን ዶላር የሚያመነጭ ሲሆን ለሰባት ሚሊዮን አፍሪካዊያን የሥራ ዕድል መፍጠሩንም የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም