መገናኛ ብዙኃን ውድድሮችን ሲዘግቡ በእውነት ላይ በመመስረት ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን ውድድሮችን ሲዘግቡ በእውነት ላይ በመመስረት ሊሆን ይገባል
አዲስ አበባ የካቲት 25/2012 (ኢዜአ) መገናኛ ብዙኃን ውድድሮችን ሲዘግቡ የዳኞችን ስብዕና በጠበቀና በእውነት ላይ በመመስረት መሆን እንደሚገባው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሳሰበ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዓቢይ ኮሚቴ የሊጉን የመጀመሪያ ዙር ግምግማ የካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም ማካሄዳቸው ይታወሳል።
ፌዴሬሽኑ ለኢዜአ በሰጠው መግለጫ እንዳመለከተውም መገናኛ ብዙኃን በሚያቀርቧቸው ዘገባዎች የስፖርት ዳኞችን ክብር በማይነካ መልኩ ሽፋን ሊሰጡ ይገባል።
ዘገባዎቻቸውም እውነትን መሠረት ያደረጉ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን የሊጉ የመጀመሪያ ዙር በተካሄደበት ወቅት ስለ ዳኞች የስፖርቱን መርህ ባልከተለ መልኩ በግምገማው ያልተነሳ ጉዳይ በማንሳት መዘገባቸው ከሙያዊ ሥነ ምግባር ውጭ እንደነበር አስታውቋል።
"መረጃው ከእውነት የራቀ፣ በውይይቱ ወቅት ያልተነሳና ተገቢነት የሌለው" እንደሆነም ገልጿል።
"ተገቢነት የሌለው መልዕክት ባለሙያውንም ሙያውንም አይለውጠውም" ያለው ፌዴሬሽኑ፣ መረጃው የዳኞችን ሞራል የሚነካ፣ የሚጎዳና ክብራቸውንም ዝቅ የሚያደርግ ነው ብሏል።
መገናኛ ብዙኃኑ ከተሳሳተ ዘገባ በመታቀብ፣ ለአገሪቱ እግር ኳስ እድገት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ፌዴሬሽኑ አሳስቧል።
የሙያን ሥነ ምግባር በጠበቀ መልኩ የእግር ኳስን ለማሳደግ ለሚሰሩ ጋዜጠኞች ያለውንም ክብር ገልጿል።