በአዲሱ ኤክሳይስ ታክስ አዋጅ አተገባበር ዙሪያ ከአምራቾች ጋር ውይይት ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ ኤክሳይስ ታክስ አዋጅ አተገባበር ዙሪያ ከአምራቾች ጋር ውይይት ተካሄደ
የካቲት 24/2012 (ኢዜአ) በአዲሱ ኤክሳይስ ታክስ አዋጅ አተገባበር ዙሪያ እየተፈጠሩ ያሉ ብዥታዎችን ሊያጠራ የሚችል ውይይት ከአምራቾች ጋር መካሄዱ ተገለጸ፡፡
ከቢራ አምራቾች ጋር የዋጋ ጭማሪና የሰራተኛ መቀነስ የውይይቱ አጀንዳዎች ናቸው ተብሏል ፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤና የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በጋራ ከአመራቾች ለተነሱት ጥያቄና አስተያየት መልስና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች መካከል የገብስ ዋጋ መጨመር በቢራ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጉ አምራቾች እንደምክንያት ያቀረቡ ቢሆንም ከመድረክ በተሰጠው ምላሽ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት የተፈጠረ በመሆኑ ከአዋጁ ጋር ግንኙት እንደሌለው ተገልጾዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ሚዲያዎች የዋጋ ንረት ሊያስከትል የሚችል የታክስ አዋጅ እንደሆነ አድርገው ቀድመው በመስራታቸው ለዋጋ መጨመር መንስኤ እንደሆነና ከአምራቾች በኩል የቢራ ማሰታወቂያ መከልከልና የተጠቃሚው ቁጥር መቀነስ ጋር ተያይዞ ለዋጋ መጨመሩ እንደምክኒያት ያነሱ ቢሆንም ይሄም ከአዋጁ ጋር እንደማይገናኝና በመንግስት በኩል የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የተወሰደ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ የታክስ ምጣኔ ከአፍሪካም ሆነ ከአለም ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን አንስተው፤ ሀገሪቱ ታክስ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን ለፋብሪካዎች ውጤታማነት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያው በምርቶች ላይ ከሚያስከትለው የዋጋ ለውጥ አንጻር ነጋዴው እያደረገ ያለው የዋጋ ጭማሪ የተጋነነ በመሆኑ ለፋብሪካዎችም ሆነ ለማህበረሰቡ ስለማይበጅ ሁሉም ሀላፊነት ተሰምቶት በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይም በገበያ ውስጥ የዋጋ ጭማሪ የሚስተዋልበት የቢራ ምርት አምራቾች ከቸርቻሪዎች ጋር በጋራ በመስራት የማስተካከል ሃላፊነት እንዳለባቸው ሚኒስትሯ አሳስበዋል፡፡
ነገር ግን ኃላፊነታቸውን በማይወጡ አካላት ላይ መንግስት ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቢዝነስ አመችነትን እየተገበረች ያለች ሀገር በመሆኗ አሁን እየተተገበረ ያለው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ በመሆኑ አምራቾች ለሚያጋጥሟቸው ችግር በጋራ ተወያይቶ መፍትሄ እየሰጡ መሄድ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ አሁን እየታየ ላለው የዋጋ ንረት ፋብሪካዎቹ ሀላፊነት ወስደው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡
የንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሼቴ አስፋው በበኩላቸው አዲስ የተተገበረው የኤክሳይስ ታክስ ከሌሎች ሀገሮችም ሆነ በተለያዩ ምርቶች ላይ የተጣለው የታክስ ምጣኔ ከፍተኛ ነው ወይ የሚለውን በሚዛናዊነት መመልክት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በአዋጁ አተገባበር ዙሪያ ግልጽነት ለመፍጠር ከሌሎች አምራቾች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ቀጣይነት እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም ለአዋጁ አተገባበር ክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር ለማድረግ ከሶስቱም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ከአምራቾች የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም ውይይቱ የተጠናቀቀ ሲሆን ለሚያጋጥሙ ችግሮች በየደረጃው የተቋቋመው ኮሚቴ በየሳምንቱና በየወሩ ተገናኝቶ መፍትሄ እንደሚየስቀምጥ መግባባት ላይ መደረሱን ከገቢዎች ሚኒስቴር ማህበራዊ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡