ቀጥታ፡

ወጣት ሴቶች ጠንካራ ራዕይ ሊሰንቁ እንደሚገባ ተፅእኖ ፈጣሪ ሴቶች ገለፁ

አሶሳ፣ የካቲት 24 / 2012 (ኢዜአ) ወጣት ሴቶች በሃገሪቱ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ራሳቸውን ከመቀየር ባለፈ ለሃገራቸው ጠንካራ ራዕይ ሊኖራቸው እንደሚገባ ተፅእኖ ፈጣሪ ሴቶች ገለፁ።

በአሶሳ ወረዳ ተገኝተው ለወጣት ሴቶች ተሞክሮአቸውን ካካፈሉ ተፅእኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል በበጎ አድራጊነታቸው የሚታወቁት ሲስተር ዘብይደር ቦጋለ፣ የኦሎምፒክ አሸናፊዋ አትሌት አልማዝ አያና ፣ ደራሲ ሜሪ ጆይ፣ አርቲስት ቻቺ ታደሰና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሴት አብራሪ ካፒቴን አምሳለ ጓሉ ይገኙበታል።

ተፅእኖ ፈጣሪ ሴቶቹ በተሞክሮ ማካፈል መድረኩ ላይ አንደገለፁት ወጣት ሴቶች መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም ራሳቸውን ከማሻሻል ባሻገር አገራቸውንና ህዝባቸውን ሊጠቅም የሚችል ራዕይ ሰንቀው ሊረባረቡ ይገባል።

በኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ተግባር ከሚታወቁት መካከል አንዷ የሆኑት ሲስተር ዘቢዳር ቦጋለ እንደሚሉት ሴቶችን ጎትተው ወደ ኋላ የሚያስቀሩ እንቅፋቶች ከቤት ይጀምራሉ፡፡

ችግሩ እርሳቸው ልጅ ከነበሩበት ጊዜ ሲነጻጸር ለውጥ ቢታይበትም አሁንም በወጣት ሴቶች ሕይወት ውስጥ ፈተና ሆነው አላንቀሳቅስ ያሉት ተግዳሮቶች ብዙ ናቸው።

ያም ሆኖ ግን ወጣት ሴቶች ተስፋ ሳይቆርጡ መታገል ከቻሉ ለስኬት እንደሚበቁ አስረድተዋል።

“ቤተሰቤን በቅንነት ከማገልገል ጀምሮ ራሴን እና ሃገሬን የመለወጥ ዓላማ ይዤ መማሬ ለውጤት አብቅቶኛል” ሲሉ የስኬታቸውን ሚስጢር አካፍለዋል፡፡

ከ30 በላይ የልጆች መጽሃፍትን ለንባብ ያበቁት ደራሲ ሜሪ ጆይ በበኩላቸው በ14 ዓመታቸው ቢዳሩም ከወለዱ በኋላ ተስፋ ሳይቆርጡ በመማር ህይወታቸውን መቀየራቸውን ይናገራሉ፡፡

“ያለማቋረጥ በማንበብ እዚህ ደርሻለሁ” የሚሉት ደራሲዋ ወጣት ሴቶች ቴክኖሎጂን ተጠቅመው የፈለጉበት መድረስ እንደሚችሉ መክረዋል፡፡

ለ25 ዓመታት በአርቲስትነት ያሳለፈችው ቻቺ ታደሰ በበኩሏ ወጣት ሴቶች በውስጣቸው ያለውን ተሰጥኦ በትምህርት በመታገዝ እንዲያወጡ መክራለች፡፡

ኢትዮጵያውን ወጣት ሴቶች ታላቅ ደረጃ በመድረስ በመላው ዓለም ሃገራቸውን እንደሚያስጠሩ አልጠራጠርም ብላለች፡፡

አትሌት አልማዝ አያና ደግሞ ወጣት ሴቶች ራሳቸውንም ሆነ ሃገራቸውን ለመቀየር ጠንክረው መማር ዋነኛው መንገዳቸው መሆን እንዳለበት አስረድታለች፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሴት አብራሪ ካፒቴን አምሳለ ጓሉ እንዳለችው ደግሞ በማህበረሰባችን ወጣት ሴቶች ሃሳባቸውን በነጻነት ከመግለጽ ይልቅ አንድ ጥግ ይዘው እንዲቀመጡ የማድረግ ልማድ አሁንም አለ ትላለች፡፡

“ጥቂት ሴቶች ጎልተን የታየነው የተለየ ነገር ሰርተን ሳይሆን ማህበረሰቡ ከሚያራምዳቸው ጎጂ ልማዶች ወጣ ብለን ስለተገኝን ብቻ ነው” ብላለች፡፡

በግሌ ማድረግ ያለብኝን ነገር ሁሉ በጊዜው ማድረግ መቻሌ እዚህ አድርሶኛል የምትለው ካፒቴን አምሳለ ወጣት ሴቶች ጊዜአቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ምክሯን ለግሳለች።

ለስኬታማነት በስነ-ምግባር መታነጽ ግድ እንደሆነም ካፒቴኗ ገልጻለች፡፡

ሁሉም ሰው ዶክተር፣ ካፒቴን፣ አትሌት እና አርቲስት ሊሆን አይችልም የምትለው ካፒቴን አምሳለ ራስን መሆን እንጂ ሌሎችን ለመምሰል መጣር አደጋ እንዳለው ታስረዳለች፡፡

ለዚህም እንደ አብነት የጠቀሰችው የፈለጉትን የመሆን አቅም እያላቸው ሌሎችን ለመምሰል ሲሞክሩ ካሳቡበት መድረስ ያልቻሉ አንዳንድ ጓደኞቿን መኖራቸውነ ጠቅሳለች

ካፒቴን አምሳለ እንደምትለው ወጣት ሴቶች በተለይም የኢንተርኔት አጠቃቀማቸው ጥንቃቄ የተሞላበት ካልሆነ ጊዜአቸውን ከማባከን ጀምሮ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስዳቸው እና ከስኬታማነት ሊያግዳቸው ይችላል፡፡

ወጣት ሴቶች አዲስ  ነገርን መፍራት እንደሌለባቸው ገልጻ ሞክረው ያልተሳካላቸው ነገር ቢኖርም እንኳን እንደገና በሌላ መንገድ ለማሳካት መጣር እንዳባቸው አስታውቃለች፡፡

lወጣት ሴቶች ህይወት አንድ መስመር ብቻ ሳትሆን በርካታ አቅጣጫዎች እንዳሏት መረዳት እንዳለባቸውም አስገንዘባለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም