ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን የማረጋገጥ መብት አላት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን የማረጋገጥ መብት አላት
ጎንደር፣ የካቲት 24/2012 (ኢዜአ) "በዓለም ዓቀፍ የተደነገገውን ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም መብት ለማረጋገጥ የሚገነባው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ጣልቃ መግባት ህጋዊ መሰረት የለውም" በጎንደር ከተማና አካባቢው የሚገኙ ምሁራንና ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የለገሷትን ወንዞች የመጠቀም መብት ለማስከበር የግድቡን ግንባታ በማፋጠን የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ማሟላት ግዴታ መሆኑን ሙሁራኑ አመላክተዋል።
"በታዛቢነት ሰበብ የአገራችን ሉአላዊነትና የህዝባችን የመጠቀም መብት የሚያደናቅፉ አገራትና ድርጅቶች የግድቡን አሞላል የሚያስቆሙበት ህጋዊ መሰረት የላቸውም" ብለዋል።
መንግስት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ የሚያደርገውን ጥረትና ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚደግፉ ምሁራኑና ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መመህር አቶ ይኼነው ምስራቅ ለኢዜአ እንደገለጹት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በእርዳታና ብድር ሳይሆን በመንግስትና በህዝብ የገንዘብ መዋጮ እየተገነባ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው።
ግድቡ የሚገነባውም አሁን በአገራችን የሚስተዋለውን የመብራት እጥረት ለመቅረፍ፣ በኢንዱስትሪ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባትና የምስራቅ አፍሪካ አገራትን በሃይል ልማት ለማስተሳሰር ነው።
ይሁን እንጂ ግብፅ ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ ግንባታውን ለማስቆምና ለማጓተት የምታደርገው ጥረት ህጋዊ መሰረት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት የግድቡን ግንባታ ፈጥኖ ለማጠናቀቅ በተያዘለት ጊዜ የውሃ ሙሌቱን መጀመርና ህዝባዊ ድጋፉን የሚያጠናክር ስራ ማከናወን እንደሚገባው አስገንዝበዋል ።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር አቶ ተፈራ እሸቱ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ህጋዊ መብቷን ማስጠበቅ የምትችለው ግድቡን በተያዘው እቅድ መሰረት ሰርታ ማጠናቀቅ ስችል በመሆኑ ለግድቡ ግንበታ መፋጠን ትኩረት መሰጠት አለበት የሚል ምክረ ሃሳብ ሰንዝረዋል ።
"አሜሪካና የዓለም ባንክ በታዛቢነት ገብተው አደራዳሪም ቢሆኑ እንኳን ለስምምነቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንጂ እኛ እናውቅላችኋለን በማለት በግዴታ የሚያስፈርሙበት ህጋዊ መሰረት የላቸውም" ብለዋል።
በአለም አቀፍ ህግ መሰረት በአንድ ተፋሰስ ያሉ ሀገራት ውሃውን በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት እንዳላቸው የተናገሩት ምህሩ ኢትዮጵያም ውሃውን የመጠቀም መብቷ የተረጋገጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የያዘውን አቋም ምሁራኑ በሙሉ ልብ እንደሚደግፉት ጠቁመው ከምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ሌላው ህዝብ ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዲካሄድ ምሁራኑ ጠይቀዋል።
በጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ በዛብህ ውለታው እንዳሉት መንግስት በዚህ ድርድር አለመሳተፉ በግድቡ ዙሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝቡ ያሳየውን የተቀዛቀዘ ድጋፍ በአዲስ መንፈስ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
"ለግድቡ ግንባታ ብድርና ድጋፍ የከለከሉ አካላት አሁን ላይ ጊዜን ጠብቀው አደራዳሪ ነን ብለው ቢቀርቡ የሚሰማቸውም ሆነ የሚያምናቸው የለም" ብለዋል።
ግድቡን ለማጠናቀቅ በገንዘብም ሆነ በሚያስፈልገው ሁሉ አስተዋጽኦ ለማድረግ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች ተናግዋል።