የምዕራብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ለሰራዊቱ አባላት የማእረግ እድገት ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የምዕራብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ለሰራዊቱ አባላት የማእረግ እድገት ሰጠ
ነቀምቴ፣የካቲት 24/2012(ኢዜአ) የምዕራብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ 124ኛውን የአድዋ ድል ምክንያት በማድረግ ለታታሪ የሰራዊቱ አባላት የማእረግ እድገት ሰጠ።
የማእረግ እድገቱ የስራ አፈጻጸም ብቃትን፣ የትምህርት ዝግጅትንና አካላዊ ብቃትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የተናገሩት የምእራብ ዕዝ የሎጂስቲክስ ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ ተመስገን ናቸው።
124ኛውን የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ምክንያት በማድረግ የማእረግ እድገቱ በተሰጠበት ወቅት ብርጋዴር ጄነራሉ እንዳሉት ሰራዊቱ የአባቶቹን ታሪካዊ የጀግንነት ተጋድሎ እንደ መልካም የህሊና ስንቅ በመቁጠር እያበረከተ ያለውን መልካም አስተዋጽኦ አጠናክሮ መቀጠል አለበት።
"ቅድመ አያቶቻችን ከኢጣሊያን ቅኝ ገዢ ኃይሎች ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ድል በነሱበት እለት ማእረግ መልበሳችሁ ቃላችሁን በድጋሜ የሚታድሱበት እለት ነውም " ብለዋል።
ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ አክለውም የማእረግ እድገቱ ለበለጠ የስራ ሞራል የሚያነሳሳችሁ በመሆኑም ኃላፊነታችሁን በቅንነትና በታማኝነት በመወጣት ውጤታማ የስራ አፈጻጸም ለማስመዝገብ መስራት አለባችሁ የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።
የእለቱ ተሿሚዎችን ያቀረቡት የምእራብ ዕዝ የሰው ኃብት መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ኡስማን አበጋዝ በበኩላቸው የመዓርግ እድገቱ የተሰጠው በየደረጃው እስከ ሙሉ ኮሎኔልነት የሚደርስ ነው።
ለ2 ሺህ 17 የሰራዊቱ አባላት ከተፈቀደው የመዓርግ እድገት መካከል 76ቱ የዕዙ ስታፍ የሰራዊት አባላት ናቸው ብለዋል።
ከማእረግ ተሿሚዎች መካከል ሌተናል ኮሎኔል በሺር ሰዒድ እንደተናገሩት ለ124ኛ ጊዜ በተከበረው በአድዋ ድል እለት ላይ ማእረግ በመልበሴ "ስራዬን በበለጠ ተነሳሽነትና ሞራል እንዳከናውን ትልቅ የህሊና ስንቅ ይሆነኛል" ብለዋል።
አክለውም ቅድመ አያቶቻችን ፋሺስት ኢጣሊያንን ዘርና ብሔር ሳይቆጥሩ በአንድነት ተዋድቀው እንደ መከቱት ሁሉ የመከላከያ ሰራዊታችን በአንድነቱ የአገራችንን ሰላም እያስጠበቀ እንደሚገኝ ገልፀው የዚህ ሰራዊት አካል በመሆኔ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል ብለዋል።
ሻምበል ገብረጊዮርጊስ ንጉሴ የተባሉ የሰራዊቱ አባል በበኩላቸው አባቶቻችን በኋላ ቀር መሳሪያ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ወራሪ ኃይል ባንበረከኩበት የድል ቀን የማዕረገ እድገት ማግኘቴ ትልቅ ሞራል ፈጥሮልኛል በማለት ገልጸዋል።