የመንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነትን መወጣት አገራዊ ምርጫን ሰላማዊ ለማድረግ ጉልህ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነትን መወጣት አገራዊ ምርጫን ሰላማዊ ለማድረግ ጉልህ ሚና አለው
ኢዜአ የካቲት 24/2012 የመንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነትን መወጣት አገራዊ ምርጫን ሰላማዊ ለማድረግ ጉልህ ሚና እንዳለው የሲቪክ ማህበራትና ድርጅቶች ገለጹ።
በዚህ ዓመት መጨረሻ የሚካሄደው ምርጫ ዓለም አቀፍ ሂደትን የተከተለ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በንቃት እንደሚሳተፉም ማህበራቱ አስታውቀዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የሲቪክ ማህበራትና ድርጅቶች መካከል የ'ሴንተር ፎር ዴሞክራሲ ኤንድ ሂውማን ራይትስ' ዳይሬክተር አቶ ዳምጤ ደመቀ እንዳሉት፤ ቀጣዩን ምርጫ ለማካሄድ መንግሥትና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ምርጫውን ለማካሃድ ከስድስት ወራት በላይ ጊዜ እንዳለው አስታውሰው፤ ''በዚህ ጊዜ ውስጥ መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት አለበት'' ብለዋል።
በመሆኑም አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የሚስተዋሉ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን መንግሥት መቆጣጠር ከቻለ፤ ምርጫውን ከመከናወን የሚያግደው ነገር እንደሌለም ያስረዳሉ።
ዜጎች የሚመራቸውን አካል የሚመርጡት በምርጫ ካርድ እንጂ፤ በሁከትና ብጥብጥ እንዳልሆነ ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፤ ''ይህንን ለኅብረተሰቡ ማስገንዘብ የመንግሥትና የሲቪክ ማህበራትና ድርጅቶች የቤት ሥራ ይሆናል'' ብለዋል።
ምርጫ ከማካሄድ ውጭ ሌላ አማራጭ ስለሌለ ለዚህም በማንነትና በዘውግ የተመሰረተ ከፋፋይ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላትን አደብ ማስገዛት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከምርጫው በፊት ለዜጎች የምርጫውን ሂደት በማስገንዘብ፤ ምርጫውን በመታዘብና ከምርጫው በኋላ ዓለም አቀፍ ደረጃውን አሟልቶ መካሄዱን በመገምገም እንደሚሳተፉም አቶ ዳምጤ አስረድተዋል።
የ'ማኅበረ ህይወት ፎር ሶሻል ዴቨሎፕመንት' ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥላዬ ግዛቸው ሰላም የሁሉም መሠረት በመሆኑ ቅድሚያ ቢሰጠውም በተጓዳኝ ምርጫውን ማካሄድ እንደሚቻል እምነታቸውን ይገልጻሉ።
ምርጫው ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ኅብረተሰቡን ከማንቃትና ከማስተማር ባለፈ፤ ፍትሃዊነቱን በማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።
በቅርቡ የተደረገው የሲዳማ ውሳኔ ህዝብ በቀጣዩ ምርጫ ለሚያደርጉት ተሳትፎ ትምህርት እንዳገኙበት ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
''በመሆኑም ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ዜጎች የሚፈልጉትን አካል በምርጫ ካርዳቸው ብቻ እንዲመርጡ ኅብረተሰቡን እናስተምራለን'' ብለዋል።