በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ በበጎ መልኩ የሚታይ መሆኑን አምባሳደር ማህቡብ ማሊም ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ በበጎ መልኩ የሚታይ መሆኑን አምባሳደር ማህቡብ ማሊም ተናገሩ
አዲስ አበባ፣የካቲት 24/2012 (ኢዜአ) ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የታየው የለውጥ ሒደት የሚደነቅና በበጎ መልኩ የሚታይ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የቀድሞ ዋና ጸሓፊ አምባሳደር ማህቡብ ማሊም ገለጹ።
ለ11 አመታት በኢጋድ ዋና ጸሓፊነት የቆዩት አምባሳደር ማህቡብ የኢትዮጵያ የቅርብ ወዳጅ መሆናቸውን ይናገራሉ።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በርከት ያለ ጊዜያቸውን በአዲስ አበባ በማሳለፋቸው የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርበት እንደሚያውቁም ይገልጻሉ።
ከዚህ ባለፈም በዚህ የኃላፊነት ጊዜያቸው ከስድስት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር በቅርበት መስራታቸውን ያስታውሳሉ።
በኢትዮጵያ የነበራቸው ቆይታም የማይረሳና ልዩ እንደነበር የሚጠቆሙት አምባሳደር ማህቡብ፤ አገሪቷ ልዩ ባህልና የተለየ ገጽታ ያላት መሆኗን ይመሰክራሉ።
በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት እየተከናወነ ያለው አጠቃላይ የለውጥ እንቅስቃሴ መልካም እንደሆነ ገልጸው፤ ''እየተካሄደ ያለው ለውጥ ፈጣንና ለማመን የሚከብዱ ተጨባጭ ሁኔታዎች የታዩበት ነው'' ብለዋል።
ሁኔታው ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት በተከታታይ ያስመዘገበችውን ፈጣን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እንድታስቀጥልም እድል የሚሰጣት የለውጥ ሂደት እንደሆነም ተናግረዋል።
በተያያዘም አምባሳደር ማህቡብ ኢጋድን በመሩበት ወቅት የፖለቲካና የቁርጠኝነት ማነስ ያሰቡትን ያህል እንዳይሰሩ እንዳደረጋቸውም ይናገራሉ።
''በቀጣናው መጥፎ ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ባህል በመዳበሩ ድርጅቱ እቅዱን በታሰበው ልክ መፈጸም አልቻልም'' ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የአገሮች የቁርጠኝነት ማነስ ኢጋድ የአቅሙን ያህል ጠንከራና ውጤታማ እንዳይሆን ማነቆ ሆኖበት መቆየቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም የተሻለ ነገር መስራት እንዲቻል የቀጣናው አገራት ጥሩ የፖለቲካ ባህል ማዳበር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
አምባሳደሩ ኢጋድ በቀጣይ በሚሰራቸው ስራዎች አዲሱን ዋና ጻሓፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን በቅርበት እንደሚያግዙም ተናግረዋል።
የስምንት የምስራቅ አፍሪካ አገራት ስብስብ የሆነው ኢጋድ ለ34 ዓመታት ገደማ በቀጣናው ላይ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።