ቀጥታ፡

ባንኩ በሴቶች የቁጠባ ሂሳብ ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ደንበኞች ከ47 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጀመረው የሴቶች ቁጠባ ሂሳብ ደብተር 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን ከደንበኞቹ ከ47 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ አሰባስቧል።

ባንኩ በሴት ሰራተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ሁለተኛ ቅርንጫፍ ከፍቷል።

ባንኩ በ2006 ዓ.ም በመጋቢት ወር የጀመረው የሴቶች ቁጠባ ሂሳብ አባላት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የባንኩ ፕሬዚዳንት ባጫ ጊና ተናግረዋል።

ዛሬ የተከፈተው የባንኩ የልደታ ቅርንጫፍ ከ40 ዓመት በላይ አገልግሎት የሰጠና ከ75 ሺህ በላይ ደንበኞች ያሉት መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ቦሌ አትላስ አካባቢ በተመሳሳይ ሴት ሰራተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡበት የመጀመሪያው ቅርንጫፍ መከፈቱንም አቶ ባጫ አስታውሰዋል።

ባንኩ ሴት ሰራተኞች ተወዳዳሪና ብቃት ያላቸው አምራች ዜጎች እንዲሆኑ ጠንክሮ እየሰራ እንደሚገኝና የቅርንጫፉ መከፈት ሴቶች ሁሉንም መስራት እንደሚችሉና ጎን ለጎን ለማብቃት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሴቶችን ለማብቃትና ለአገር የሚኖራቸውን ድርሻ ለማሳደግ እንዲሁም በንግድ፣ በሀብት ፈጠራ፣ በአምራች ኢንዱስትሪና ግብርና ዘርፎች እያከናወኑ ያሉትን ስራ ለማገዝ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

በርካታ ሴቶች በተለያዩ የባንኩ የአመራር እርከኖች ተመድበው በብቃት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ባንኩ የሴቶችን የፋይናንስና ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጎልበት በማቀድ የቁጠባ ሒሳብ አገልግሎት እንዲጀመር ማድረጉን ገልጸዋል።

በፕሮግራሙ  ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ የከተማ ግብርና ኮሚሽነር ወይዘሮ ፈቲያ መሐመድ እንዳሉት፤ ሴቶች ከራሳቸው አልፈው የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት የበለጠ ተግተው መስራት አለባቸው።

ሴቶች በፈተና ውስጥ አልፈው ለበለጠ ስኬት ለመብቃትና ለአገራቸው የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ የባንኩ ሴት ሰራተኞች ለላቀ ስራ እንዲነሳሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የቅርንጫፉ ስራአስኪያጅ ወይዘሮ ሉሲ ተስፋዬ በበኩላቸው የቅርንጫፉ መከፈት እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ በቀጣይ ለበለጠ ስራ እንደሚተጉ ተናግረዋል።

''የቅርንጫፉ ሴት ሰራተኞችም እንደምንችል ለማሳየት በትኩረት እንሰራለን'' ብለዋል።

በተመሳሳይ በየዓመቱ የሚከበረውን የሴቶች ቀን 'ማርች 8' የባንኩ ሴት የስራ ሃላፊዎችና የባንኩ ፕሬዚዳንት ባጫ ጊና በተገኙበት ተከብሯል።

ባንኩ በ77 ዓመታት ቆይታው በመላ አገሪቱ 1 ሺህ 560 ቅርንጫፎች አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም