ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሀዊ የሚሆነው ህዝቡ በነጻነት መምረጥ ሲችል ነው - አስተያየት ሰጪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሀዊ የሚሆነው ህዝቡ በነጻነት መምረጥ ሲችል ነው - አስተያየት ሰጪዎች
ኢዜአ የካቲት 24/2012 በመጪው ነሐሴ የሚካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሀዊ የሚሆነው ህዝቡ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በነጻነት መምረጥ ሲችል እንደሆነ ተገለጸ።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ዜጎች ለሚፈልጉት ፓርቲ ድምጽ እንዲሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን በአግባቡ ማስተዋወቅ ይኖርባቸዋል።
ከዚህ ውጪ በሆነ መንገድ ዜጎች ድምጽ እንዲሰጡ ማድረግ የምርጫውን ሰላማዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነት ነጻነት የሚጋፋ መሆኑን አመልክተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅትም ሕግና ስርዓትን ተከትለው ሊሆን እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ምርጫ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ለማካሄድ ቀን መቁረጡ ይታወቃል።
ምርጫው ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ ምርጫዎች በተሻለ መልኩ እንዲካሄድ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለባቸው አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል።
በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመራጩ ህዝብ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር ድርጊት ማከናወን እንደማይገባቸው አስገንዝበዋል።
የባህር ዳር ከተማ ነዋሪው አቶ ሙሉጌታ ዓለሙ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፤ ሕዝቡ ከተጽዕኖ ነጻ ሆኖ መምረጥ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት።
''ለዚች አገር ሁሉም ኃላፊነት አለበት'' ያሉት አቶ ሙሉጌታ ፓርቲዎችም 'የኔ ፓርቲ ብቻ ይመረጥ' ከማለት መቆጠብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት አማረ አየነው በበኩሉ መንግሥት በተደጋጋሚ እንደሚናገረው ምርጫው ፍትህሃዊ እንዲሆን ተጨባጭ ተግባር ያስፈልጋል።
''ሕዝቡ ፍትሃዊ ሁኔታ ከተመቻቸለት ከመምረጥ ወደኋላ አይልም'' ሲልም ገልጿል።
''አገር ከሌለ ምርጫ የሚባል ነገር አለመኖሩን በመገንዘብ የምርጫው ተዋንያን በውይይት መጓዝ ይኖርባቸዋል'' ያሉት ደግሞ ወታደር ሞልቶ ታደለ ናቸው።
ሰላማዊ የሆነ ሁኔታ እንዲፈጠርም መስራት የሁሉም ግዴታ እንደሆነ አመላክተዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት መልካሙ ተሾመ በበኩሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቀስቀሳ ሲያደርጉ ህግና ስርዓት ተከትለው መሆን እንዳለበት ጠቁሟል።
ወጣት ሳሮን ዓለሙም መጪው ምርጫ ሁሉም የሚበጀውን ፓርቲ ለመምረጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ በተረጋጋ መንፈስ የሚወስንበት ነው በማለት ሀሳቧን አጋርታለች።
የህዝቡ ፍላጎት ሰላም መሆኑን በመረዳት ፖለቲከኞች ሃሳባቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ዓላማቸውን ማስረዳት እንዳለባቸው ተናግራለች።
ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ የማስፈጸሚያ መመሪያ ከማውጣት ጀምሮ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።