ቀጥታ፡

በጀርመኑ የታዳጊዎች እግር ኳስ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተጫዋቾች ታወቁ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2012 (ኢዜአ) የጀርመኑ እግር ኳስ ክለብ ባየርሙኒክ በሚያዘጋጀው የታዳጊዎች እግር ኳስ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉት ተጫዋቾች ዝርዝር ይፋ ሆኗል።

ዘጠነኛው የባየርሙኒክ የታዳጊዎች እግር ኳስ ውድድር ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን በውድድሩ ከ14 እስከ 16 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ታዳጊዎች ይሳተፉበታል።

በውድድሩ ኢትዮጵያን የሚወክለውን ቡድን ለመምረጥ የካቲት 19 እና 20 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ከ16 ዓመት በታች የታዳጊዎች ውድድር ተካሂዷል።

በምርጫ ውድድሩ ላይ ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ 16 ቡድኖች የተሳተፉ ሲሆን እያንዳንዱ ቡድን 10 ተጫዋቾችን የያዘ ነው።

በውድድሩ ከተሳተፉት 160 ተጫዋቾች መካከል የተሻለ ብቃት ያላቸው 10 ተጫዋቾች መመረጣቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወጣት ክፍል ባለሙያ አቶ ያሬድ አለማየሁ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የተመረጡት ተጫዋቾች ቢንያም ንጉሴ፣ ፉአድ አብዱራህማን፣ አሸናፊ አስፋው፣ ጀማል መሐመድ፣ አቡበከር አክሊሉ፣ ያሬድ አበራ፣ ትንሳኤ ሽፈራው፣ ሄኖክ ካሳ፣ ናታን ንጉሴና አስጨናቂ ገበያው ናቸው።

የባየርሙኒክ የታዳጊዎች አሰልጣኝ ክሪስ ሎክና ላርስ ዊቻርት ተጫዋቾችን መምረጣቸውን ነው አቶ ያሬድ የጠቆሙት።

በሁለቱ ቀናት ውድድር እያንዳንዱ ቡድን አምስት ጊዜ መጫወቱንና ይሄም ተጫዋቾቹን በተደጋጋሚ በማየት የተሻሉትን ለመምረጥ አሰልጣኞቹ የተከተሉት ስልት እንደሆነ ጠቁመዋል።

የባየርሙኒክ የታዳጊዎች አሰልጣኞች የተከተሉት የውድድር አቀራረብ ይዘት ተሞክሮ የሚወሰድበትና በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በአነስተኛ ወጪ ማካሄድ የሚቻል እንደሆነም አመልክተዋል።

በውድድሩ ጥሩ ብቃት የሚያሳዩ ተጫዋቾች የባየርሙኒክ የእግር ኳስ አካዳሚን የመቀላቀል ዕድል እንደሚኖራቸው አክለዋል።

በቀጣይ ተጫዋቾችን የሚመራ አሰልጣኝ እንደሚመርጡና በዚህም በአዲስ አበባ በሰጡት የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ከተሳተፉ አሰልጣኞች የተሻለ ብቃት ያለውን ሊመርጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

በዘጠነኛው የባየርሙኒክ የታዳጊዎች ውድድር ኢትዮጵያን ጨምሮ ከጀርመን፣ ታይላንድ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቶጎ፣ ናይጄሪያ፣ ኦስትሪያና ጃፓን የተውጣጡ ቡድኖች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም