የአርባምንጭ ከተማ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በደደቢት ተጫዋቾች ላይ የተገቢነት ክስ አቅርቧል

72
አዲስ አበባ ሰኔ21/2010 የአርባምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በደደቢት ተጫዋቾች ላይ የተገቢነት ክስ ማቅረቡን አስታወቀ። ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ደደቢት አርባምንጭ ከተማን ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ማሸነፉ የሚታወስ ነው። "ለደደቢት የተሰለፉት ስዩም ተስፋዬና አቤል ያለው በጨዋታው ላይ አምስት ቢጫ እያለባቸው መሰለፋቸው የስነ ምግባር ደንብ የሚጥስ በመሆኑ" ክለባቸው ለፌደሬሽኑ የተገቢነት ክስ በደብዳቤ ማቅረቡን የአርባምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የቡድን መሪ አቶ ዋለልኝ ዮሐንስ ለኢዜአ ገልጸዋል። "ሁለቱ ተጫዋቾች በጨዋታው ላይ አምስት ቢጫ በማግኘታቸው መሰለፍ እንደሌለባቸውና ቅጣታቸውን በወቅቱ ለፌዴሬሽኑ አለመክፈላቸውን የሚያሳይ መረጃ ክለቡ አለው" ብለዋል። እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የተጫዋቾቹን ተገቢነት በማጣራት የተመዘገበውን ውጤት መቀየር እንዳለበት ነው አቶ ዋለልኝ የተናገሩት። የአርባምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ያቀረበውን የተገቢነት ክስ በማጣራት የስነ ምግባር ኮሚቴ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ መለክታል። የአርባምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የተጫዋች ተገቢነት ክስ ተቀባይነት ካገኘ የደደቢት ውጤት ተቀልብሶ አርባምንጭ ከተማ በፎርፌ 3ለ0 አሸናፊ እንዲሆንና ሶስት ነጥብ እንዲያገኝ ይደረጋል። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሃ ግብር በይርጋለም ስታዲየም በሲዳማ ቡናና አዳማ ከተማ መካከል በተደረገው ጨዋታ ሲዳማ ቡና 1ለ0 አሸንፎ ነበር። በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ብቸኛውን ግብ ያስቆጠረው አዲስ ግደይ አምስት ቢጫ እያለበት በጨዋታው ላይ ተሰልፏል። የፌዴሬሽኑ የስነ ምግባር ኮሚቴ ጉዳዩን በማጣራት ሲዳማ ቡና በጨዋታው ላይ አግባብነት የሌለውን ተጫዋች በማሰለፉ የሲዳማን የአሸናፊነት ውጤት በመቀልበስ አዳማ ከተማ በፎርፌ 3ለ0 አሸናፊ እንዲሆንና ሶስት ነጥብ እንዲያገኝ መወሰኑ የሚታወስ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም