ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ውድድር በደቡብ ክልል አሸናፊነት ተጠናቋል

አዲስ አበባ ሰኔ21/2010 የደቡብ ክልል በኢትዮጵያ ቮሊቦል የ2010 ዓ.ም ውድድር በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ በመሆን አጠናቀቀ። ከሰኔ 14 ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ፍጻሜውን አግኝቷል። በውድድሩ ላይ በወንዶች ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብና ትግራይ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተሳትፈዋል። በሴቶች ደቡብ፣ ትግራይና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተሳትፈዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚና የአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ውድድሩን ያስተናገዱ ስፍራዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት በቮሊቦል ስፖርት ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራትና በሁለቱም ጾታዎች በሚካሄደው የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ብቁ ተጫዋቾችን መመልመል የውድድሩ ዋነኛ ዓላማ ነው። በተጨማሪም ስፖርቱ በህብረተሰቡ ዘንድ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረውና እንዲስፋፋ ለማድረግ ውድድሩ  የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተናግረዋል። በውድድሩ ላይ ሁሉም ክልሎች እንዲሳተፉ ፌዴሬሽኑ ጥሪ ቢያቀርብም ስድስት ክልሎች በበጀት እጥረት ምክንያት አለመሳተፋቸውን አመልክተዋል። ዛሬ በተደረገው ጨዋታ በወንዶች ደቡብ ክልል በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ሶስት ለዜሮ ያሸነፈ ሲሆን ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር የሌለውና የአንድ ቡድን ብቻ የበላይነት የታየበት ነበር። አዲስ አበባ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የትግራይ ክልልን ሶስት ለአንድ አሸንፏል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ሲሆን በትንሿ ስታዲየም የተገኘውን የስፖርቱን አፍቃሪ ቀልብ የሳበ ነበር። በዚህም መሰረት በወንዶች ደቡብ ክልልና አዲስ አበባ ተመሳሳይ አስር ነጥብ ቢኖራቸውም የደቡብ ክልል በውድድሩ መመሪያ መሰረት የተሻለ የዙር ጨዋታ በማሸነፉ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልሟል። አዲስ አበባ ሁለተኛ፣ ትግራይ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። በሴቶች የደቡብ ክልል ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች በማሸነፍ በዘጠኝ ነጥብ አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ አግኝተዋል። ትግራይ ሁለተኛ፣ አዲስ አበባ ሶስተኛ በመውጣት የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸልመዋል። አሰልጣኝ ታፈሰ መና እና አሰልጣኝ አየለ ሊራሞ ከደቡብ ክልል በቅደም ተከተል የሴትና የወንድ ቡድን ኮከብ አሰልጣኝ በመሆን የሜዳሊያ ሽልማት አግኝተዋል። በሴቶች የደቡብ ክልሏ ተጫዋች ታመነች ታንቱ፣ በወንዶች የትግራይ ክልሉ ተጫዋች ብርሃነ ረዳይ ኮከብ ተጫዋች በመሆን የሜዳሊያ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። በሴቶች የትግራይ ክልል በወንዶች የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጸባይ ዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል። በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ የሆነው የደቡብ ክልል የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል። የደቡብ ክልል አሸናፊ በመሆኑ ካገኘው የዋንጫ ሽልማት በተጨማሪ በቀጣይ ዓመት በሁለቱም ጾታዎች በኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ቡድኖችን የማሳተፍ እድል አግኝቷል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽንና የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ለተወዳዳሪዎች የተዘጋጀውን ሽልማት አበርክተዋል። የቮሊቦል ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ የገባው አገሪቱ ዘመናዊ ትምህርትን ማስፋፋት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ሲጀምር በአብዛኛው በውጭ መምህራን ስለነበር መምህራኑ ስፖርቱንም እንዳስጀመሩት በዘርፉ የተደረጉ ምርምሮች ያሳያሉ። የስፖርቱ መዘውተር በ1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን እንዲመሰረት አስችሏል። ከ1980ዎቹ በኋላ መጠነኛ መቀዛቀዝ ያሳየው የኢትዮጵያ ቮሊቦል ስፖርት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ ቀድሞ ለመመለስ በወንድም በሴትም የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ማካሄድን ጨምሮ የተለያዩ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም