ቀጥታ፡

የአድዋ የድል ታሪክ በድህነት ላይም ሊደገም ይገባል…የጎንደር ከተማ አስተዳደር

(ጎንደርና ደብረብርሃን ኢዜአ)...ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በህብረት ቀኝ ገዥዎችን እንዳንበረከኩ ሁሉ የአሁኑ ትውድልም አንድነቱን ጠብቆ ድህነትን ድል በማድረግ የራሱን ታሪክ ሊሰራ እንደሚገባ የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ ገለፁ።

የ124ኛው የአድዋ ድል በዓል በጎንደርና በደብረ ብርሃን ከተሞች ዛሬ በድምቀት ተከብሯል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ማስተዋል ስዩም በበዓሉ ላይ እንዳሉት አባቶች በጠላት ላይ የሰሩት አኩሪ ገድል ኢትዮጵያውያን በአለም ፊት አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲጓዙ ያደረገ ነው።

"የአድዋን የድል በዓል ከማክበርና ከመዘከር ባለፈ የአሁኑ ትውልድ ድህነትንና ዘረኝነትን በመዋጋት ለሃገሩ ቆይቶ ሊነገር የሚችል ታሪክ መስራት ይገባዋል"ብለዋል።

"የቀጣይ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ የሚወሰነው የአሁኑ ወጣት ሃይል በሚሰራው ስራ ነው" ያሉት ምክትል ከንቲባው አባቶች ለውጭ ወራሪ ያልተደፈረች ሀገርን እንዳስረከቡ ሁሉ ወጣቶችም የበለፀገች ሃገርን ማስረከብ የግድ እንደሚላቸው አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ በበኩላቸው "አድዋን ስንዘክር ለሀገር ክብርና ነፃነት በአንድነት የተዋደቁትን አባቶቻችንን ታሪክ ለመጠበቅና ከእነሱም ለመማር ነው" ብለዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድም ምንም እንኳን የውጭ ወራሪ ባይኖርም ከድህነት ጋር ቆራጥ ትግል በማድረግ ማሸነፍ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

በጎንደር የአባት አርበኞች ማህበር ተወካይ አቶ አስማረ አባይ በበኩላቸው "አያቶቻችን የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ቀንዲል እንደሆኑ ሁሉ ወጣቱ ትውልድ ለአለም ህዝቦች የአንድነትና የፍቅር ተምሳሌት መሆን ይገባል" ብለዋል።

በተመሳሳይም በደብረብርሃን ከተማ በተከበረው በዓል ላይ የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ብርሀኑ ታየ እንደተናገሩት ጀግኖች አያቶቻችን አድዋ ላይ ያስመዘገቡትን ድንቅ ታሪክ የአሁኑ ትውልድም የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ በማሳካት በራሱ ድል ሊኮራ ይገባል።

የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ትእግስት መኳንንቴ በበኩላቸው የአደዋን የድል ታሪክ ጠብቆ ለትውልድ ከማቆየት ባለፈ የጥንቱን የጀግንነት ገድል በድህነት ላይ ለመድገም ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአደዋ ድል የህዝብ ድል እንደመሆኑ የዘመኑ ትውልድም የራሱን ታሪክ እንዲሰራ በጋራና በአብሮነት መንቀሳቀስ እንዳለበት አስረድተዋል።

በሁለቱ ከተሞች በተከበረው 124ኛው የአድዋ የድል በዓል ላይ አባት አርበኞች፣ ወጣቶችና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም