ቀጥታ፡

የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊ ስሜትን በማጠናከር ለጋራ ብልፅግና መረባረብ ያስፈልጋል ተባለ

ሰመራ፣ የካቲት 23/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ከአድዋ ድል ለጋራ ዓላማ ተባብሮ በአንድነት መቆምን ወርሰን ለአገራዊ ብልፅግና መረባረብ እንደሚገባን የአፋር ክልላዊ መንግስት ገለፀ ።

በክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሺን ጽህፈት ቤት መላው ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለ124ኛው የአድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ የሚል የመልካም ምኞት መግለጫ መልእክት ተላልፏል ።

ጀግኖች አባቶቻችን የሀገራቸውን  ሉአላዊነት  ለማስከበር የብሄርና የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው በአንድነት ተሰልፈው በደማቸው ዘመን ተሻጋሪ ደማቅ ታሪክ የጻፉበት እለት መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

አፍሪካዊያንና መላው ዓለም ካስደመመው ተጋድሎ አንድነትን ፣ መተባበርንና ለጋራ ዓላማ በጋራ መቆምን ለድል እንደሚያበቃ ልንማርበት እንደሚገባም ተጠቅሷል ።

የአፋር ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን የታሪካዊው የአድዋ ድል ባለቤት እንደሆነ ሁሉ አሁንም አንድነቱን አጠናክሮ በፀረ ድህነት ትግሉ እንደሚደግመው በመግለጫው አረጋግጧል ።

በአድዋ ድል የታየውን የህዝቦች የተባበረ ክንድ ይዘን በህብር ወደ ብልፅግና ማማ እንወጣለን ሲልም ክልሉ በመግለጫው አትቷል ።

የአፋር ህዝብና መንግስት ዛሬም እንደ ትናንቱ በሀገሩ ሁለንተናዊ ልማትና ዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ላይ  ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችጋር በጋራ በመሆን ድሉን ለመድገም ዝግጁ መሆኑም ተገልጿል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን አጠናክሮ ለሁለንተናዊ ብልፅግና የበኩሉን ገንቢ ሚና እንዲጫወትም የክልሉ መንግስት ጥሪውን አስተላልፏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም