የአድዋ ድል የአንድነታችን ካስማና የነጻነታችን ምንጭ ነው---ዶክተር ፍሬው ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል የአንድነታችን ካስማና የነጻነታችን ምንጭ ነው---ዶክተር ፍሬው ተገኘ
ባህርዳር የካቲት 23/2012 "የአድዋ ድል የአንድነታችን ካስማና የነጻነታችን ምንጭ በመሆኑ ታሪኩ በአግባቡ ተቀምሮ ለመጪው ትውልድ ሊተላለፍ ይገባል" ሲሉ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ አስታወቁ።
124ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
ዶክተር ፍሬው ተገኘ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ጀግኖች አባቶች ወንዝ ተሻግሮ የመጣው የኢጣሊያን ወራሪ ኃይል በመደምሰስ የሀገሪቱን ሉአላዊነት አስከብረዋል።
ኢትዮጵያዊያን የንጉስ ሚኒሊክን ጥሪ ተቀብለው በአንድነት መንፈስ ወደ አድዋ በመዝመታቸውና ተዋግተው በማሸነፋቸው ዛሬ አንገታችን ቀና አድርገን በኩራት እንድንራመድ አስችሎናል ብለዋል።
በአባቶች ተጋድሎ የተገኘው የአድዋ ድል ለመላው የአፍሪካ ጥቁር ህዝብና በሌላው ዓለም በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩ ሀገራት የጸረ ቅኝ ትግል መንገድ የከፈተና ፋና ወጊ ሆኖ አገልግሏል።
እንደ ዶክተር ፍሬው ማብራሪያ ለድሉ መገኘትም የአርበኞች የሃገር ፍቅር፣ ቆራጥነት፣ አንድነት፣ ጽናትና ሀገርን በውጭ ወራሪ ላለማስደፈር ካላቸው ጽኑ እምነት የመነጨ ነው።
" ድሉ የአንድነታችን ካስማና የነጻነታችን ምንጭ በመሆኑ ታሪኩ በአግባቡ ተቀምሮ ለመጪው ትውልድ ሊተላለፍ ይገባል" ብለዋል።
የዚህ ዘመን ትውልድም አሁን እንደ ሃገር የገጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የአባቶች ጥበብ ሊጠቀምበት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአድዋ ድል ታሪክን በማጥናትና በመመርመር ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቀዋል።
በአማራ ክልል የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዳኝነት አያሌው በበኩላቸው በተለያዩ ዘመናት የውጭ ወራሪዎች ሀገሪቱነ ለመቀራመት ቢሞክሩም በአባቶች ጀግንነት ሊከሽፍ እንደቻለ አውስተዋል።
ከ25ሺህ በላይ ዘመናዊ የጣሊያን ጦርም መድፍ፣ መትረየስና ሌሎች ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ታጥቆ ድንበር አቋርጦ መጥቶ እንደነበር አስታውሰው "ኢትዮጵያዊያን በጀግንነት በአድዋ ተራሮች ስር ተቀብሮ እንዲቀር ሆኗል " ብለዋል።
የማህበሩ ፕሬዚደንት እንዳሉት ከሰባት ሺህ በላይ የጣሊያን ወታደሮችና ቅጥረኞች ሲሞቱ ቀሪው ምርኮኛና ሸሽቶ ወደ መጠባት እንዲመለስ ያደረግ ታላቅ ድል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
የአሁኑ ትውልድም አባቶቹ መስዋዕትነት ከፍለው ያስረከቡትን ሃገር ለጥፋት በተሰለፉ አካላት እንዳትፈርስ በጽናት ታግሎ ማሸነፍ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ "ለዘመናት የዘለቀው የነጭ የበላይነትንና የጥቁር የበታችነትን ታሪክ ያፈራረሰው የአድዋ ድል ነው" ብለዋል።
የአሁኑ ወጣትም ከዚህ አኩሪ ታሪክ ልምድ በመውሰድ የሚስተዋለውን የቅኝ ገዥዎች ሴራ ለማክሸፍ በጋራ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።
በዓሉ በባህርዳር ከተማ የተከበረው በፓናል ውይይት ፣ በዋና ዋና አደባባዮች ሰልፍ ፣ የፉከራና ሽለላ ትርኢቶች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ጥበብ ህንጻ አዳራሽ የተለያዩ ዝግጅቶች በማቅረብ ነው።