ቀጥታ፡

"የአድዋ ድል ዛሬም ለኢትዮጵያዊያን የመተባበር ተምሳሌት ሆኖ ይወሰዳል"

አዲስ አበባ የካቲት 21/2012 (ኢዜአ)  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአድዋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። 

አስተያየት ሰጭዎቹ የአድዋ ድል የጽናትና የጀግንነት ተምሳሌት ሆኖ ዛሬ ላይ እየተከበረ እንዳለ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ የልማት ጀግና መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

በመሆኑም ለግድቡ ግንባታ ዳር መድረስ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል ታጋይ ሃለቃ ዜና ገብረ ተንሳይ በግድቡ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት መሳተፉን ጠቅሰው ግድቡ የሚገጥሙትን ማናቸውንም የአገር ውስጥና የውጭ ተፅዕኖዎችን በፅናትና በአንነድነት ልናልፋቸው ይገባል ብለዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ በሪሁን ገብረ መድህን ኢትዮጵያ በወቅቱ ገጥሟት የነበረውን የጣሊያን ወራሪ ሃይል ያሸነፈችው በነበራት የጦር ሃይል ወይም የተማረ የሰው ሃይል ሳይሆን በነበራት የአንድነት እንደነበር አንስተዋል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ቆመን መስራት አለብን ብለዋል።

በግድቡ ግንባታ ሂደት ለሚገጥሙ ችገሮች ሁሉ በጋራ እየመከርን መፍትሄ እያስቀመጥን መሄድም ከመላ ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅ መሆኑንም አስረድተዋል።

በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚደረገው ድርድርም ሆነ ስምምነት የሃገርን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስከብር መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለብንም ለአድዋው ጦርነት እንደ ምክንያት ከሚነሳው የውጫሌ ስምምነት ልንማር ይገባል ብለዋል።

የአክሱም ዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነው አወል ሙሰማ በበኩሉ የአድዋ ድልና የህዳሴው ግድብ ሁለቱም የሃገር ሉአላዊነት ጉዳይና የኢተዮጵያዊያንን የጋራ ውሳኔ የሚሹ ናቸው ሲል ተናግሯል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሉአላዊነትና የህልውና ጉዳይ መሆኑን አስተያየት ሰጭዎቹ ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁናዊ አፈፃፀሙ ከ70 በመቶ በላይ መድረሱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም