ትውልዱ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን በማጠናቀቅ አርበኝነቱን በተግባር ማሳየት አለበት ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን በማጠናቀቅ አርበኝነቱን በተግባር ማሳየት አለበት ተባለ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 23/ 2012 ( ኢዜአ) የአሁኑ ትውልድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በማጠናቀቅ አርበኝነቱን በልማትና በተግባር ሊያሳይ እንደሚገባ ተገለጸ።
የሕዳሴው ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ በአርበኝነት ስሜት የድርሻቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በአዲስ አበባ የአድዋ ድል በዓል ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
124ኛው የአድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ በድምቀት ተከብሯል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎች በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ግድቡ ልክ እንደ አድዋ ድል የአንድነት ተምሳሌትና የአገር ፍቅር ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
የሌሎች አገሮች ጣልቃ ገብነትም ሆነ ማስፈራርያ ግድቡን ከማጠናቀቅ ወደ ኋላ የሚያስቀር አለመሆኑንም ነው የገለጹት።
አቶ ደመላሽ ካሳዬ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ መነሻ እንደ መሆኗ በውሃው የመጠቀም ሙሉ መብት አላት ባይ ናቸው።
አገሪቷ ከሌሎች አገሮች ጋር በፍትሃዊነትና በትብብር የዓባይን ውሃ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ አቋሟን ስትገልጽ መቆየቷን አስታውሰው ፤ በተለይ የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
አቶ ዳኜ ይርዳው የተሰኙ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው "ግድቡ በአገር ውስጥ አቅምና በዜጎች ትብብር የተጀመረ እንደመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ የማየት ህልም አለው" ይላሉ።
ይህን ህልሙን እውን ለማድረግም በቻለው ሁሉ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።
''በአገር ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠረው ልዩነትና መከፋፈል በሕዳሴ ግድብ ላይ አይሰራም'' የሚለው ደግሞ ወጣት ብርሃኑ በላይ ነው።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዓባይና በሕዳሴ ግድቡ ላይ ወደ ኋላ የሚያፈገፍግበት ምክንያት ባለመኖሩ ግድቡን በማጠናቀቅ የጥንት አርበኞችን ታሪክ ለመድገም ዝግጁ ሊሆን ይገባል ብሏል።
"የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ወጣቶች በቁርጠኝነት ስሜት ሊሰሩ ይገባል" ሲል የወጣት ብርሃኑን ሀሳብ የተጋራው ደግሞ ወጣት አበባ ፈይሳ ነው።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአቅሙ አስተዋጽኦ በማድረግ ግድቡን ለመገንባት ቃል በገባው መሰረት ግንባታው ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ እስኪውል ድረስ ወደ ኋላ ማለት እንደሌለበትም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።
ግንባታው ከተጀመረ ዘጠኝ ዓመታትን ያስቆጠረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁን ላይ 70 በመቶ አፈፃፀም ላይ ደርሷል።