ቀጥታ፡

ወጣቶች ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደም የአባቶችን ገድል መድገም እንዳለባቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ የካቲት 23/2012 (ኢዜአ)  ወጣቶች የአገርን አንድነት ከሚከፋፍሉ አስተሳሰብ በመታገል ኢትዮያዊነትን በማስቀደም የአባትና እናቶችን ገድል መድገም እንዳለባቸው የአድዋ ድል በዓል ተሳታፊዎች ገለጹ።

124ኛው የአድዋ የድል በዓል በአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ በድምቀት ተከብሯል።

ከአዲስ አበባ ተለያዩ አካባቢዎች ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ የተገኙ ታዳሚዎች በዓሉን በአገር ባህል አልባሳት ተውበው በሽለላና ቀረርቶ እንዲሁም በሌሎች ዝግጅቶች አክብረውታል።

ከታዳሚዎቹ መካከል ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ እንዳሉት ጀግኖች አባቶችና እናቶች የአድዋን ጦርነት ድል ያደረጉት ዘር፣ ሃይማኖትና ጾታ ሳይለዩ ባደረጉት ተጋድሎ ነው ብለዋል።

መሆኑንም የአሁኑ ትውልድ የአቶችና እናቶቹን አኩሪ ታሪክ ከሚያጠለሹና ከሚከፋፍሉ ተግባራት እንዲቆጠብ መክረዋል።

የዘመኑ የኢትዮጵያ ዋነኛ ጠላት ድህነት መሆኑን አንሰተው ይህን ለማሸነፍ ደግሞ አገራዊ አንድነትን ከሚሸረሽሩና ከሚከፋፍሉ ተግባራት መቆጠብ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ወጣት ፍጹም ተፈራ እንደሚለው ጀግኖች አባቶች በዘርና በሃይማኖት ሳይከፋፈሉ በአንድነት ስሜት የአገርን ክብርና ሉዓላዊነት አስጠብቀው ቆይተዋል።

"ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገሪቷ እየታየ ያለው የዘረኝነት መንፈስ ይህን አኩሪ ታሪክ የሚያጠለሽ በመሆኑ በተለይ ወጣቱ የአንድነት ስሜቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል አድዋን ትልቅ ምሳሌ ማድረግ ይኖርበታል" ብሏል።

"ተማሪውም ሆነ ሰራተኛው በተሰማራበት መስክ ጠንክሮ በመስራት ለአገሩ ዕድገትና ብልጽግና የድርሻውን ሊወጣ ይገባል" ያለችው ደግሞ ወጣት ገሊላ ዓለምሰገድ ናት።

አድዋ የአልበገር ባይነትና የጀግነነት ተምሳሌት በመሆኑ አገሪቷን እየተፈታተነ ያለውን ድህነት ለማሸነፍ የዘረኝነትን አስተሳሰብ ማቆም ይገባል ብላለች።

ወጣት ሙሉቀን አሰፋ በበኩሉ መለያየትና መከፋፈል ለየትኛውም አገር ልማትና ብልጽግና የማይበጅ መሆኑን ጠቅሶ፣ ትውልዱ በአገር ፍቅር ስሜትና በትብብር መንፈስ የተሻለች አገር በመገንባት የአባቶቹን ድል ሊደግም እንደሚገባ ነው የተናገረው።

የአርበኛ ልጅ ወይዘሮ የህዝብዓለም ነጋ በበኩላቸው ወጣቱ የአባትና እናቶቹን የድል ታሪክ መዘከሩ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

"ይሁንና ሁሌ ታሪክ ዘካሪ ብቻ ሳይሆን የራሱን ታሪክ ሰርቶ ለተተኪ ትውልዶች ማስተላለፍ እንዲችል ከወዲሁ በየተሰማራበት ዘርፍ መትጋት አለበት" ብለዋል።

አርበኝነት "ጦረኝነት" ብቻ አለመሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ የህዝብዓለም በትምህርትና በተሰማሩባቸው ሌሎች የስራ መስኮችም አርበኛ መሆን ይቻላል ብለዋል።

በመሆኑም ወጣቶች ለአገራቸው ዕድገት የድርሻቸውን ለመወጣት ሁሌም ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም