ቀጥታ፡

ለሕዳሴው ግድብ ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነን - ነዋሪዎች

 አዲስ አበባ የካቲት 21/2012 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚጠየቀውን ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ኢዜአ ያነጋገራቸው ዜጎች ተናገሩ።

የኢዜአ ሪፖርተር በአማራ ክልል ደሴና ማጀቴ ከተሞች እንዲሁም በትግራይ ክልል ኮረም ከተማ በመገኘት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

በአስተየታቸውም ለግድቡ ግንባታ ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የገለጹት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ህልውና በመሆኑ  በአንድ ላይ የሚቆሙለት የጋራ ሃብታቸው መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ግድቡ እስከ ህይወት መስዋዕትነት የሚከፍሉለት የአንድነትና የጋራ ህልውና መሆኑንም ገልጸዋል።

አስተያየት ሰጭዎቹ "የግድቡ ግንባታ የሚገጥሙት መሰናክሎች ቢኖሩ እንኳን በጋራ ቆመን ችግሩን ለመፍታት ተዘጋጅተናል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት የውሃ ተጠቃሚነት ሳይጎዳ በአባይ ወንዝ ላይ የራሱን ጥቅም ለማስከበር የያዘውን አቋም አድንቀዋል።

በትግራይ ክልል ኮረም ከተማ የሚኖረው ወጣት ብርሃኑ ከላኢ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሚያስገኘው የኢኮኖሚ ጥቅም በተጨማሪ ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ላይ አስተባብሮ ያሰለፈ መሆኑ ተናግሯል።

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየገጠማት ለመጣው የዘር እና የሃይማኖት አክራሪነት ችግሮችን ለመፍታት እንደ ሕዳሴው ግድብ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን አመልክቷል።

"የሕዳሴው ግድብ ሁላችንም በጋራ የምንቆምለትና አስፈላጊውን መስዋዕትነት የምንከፍልለት ነው" ሲልም ተናግሯል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ማጄቴ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት አሳልፈው ረታ ደግሞ ግድቡ ኢትዮጵያዊያንን ከጫፍ ጫፍ ያሰተሳሰረ እና በጋራ የቆምንለት ሃብታችን ነው ብሏል።

በግንባታ ሂደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮች ቢኖሩ እንኳን በጋራ የጀመርነው በመሆኑ ችግሩን በትብብር እንፈታዋለን ብሏል።

የደሴ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሃና ጌታቸው በበኩሏ "ግድቡ የአገራችን መፃኢ ተስፋና የዚህ ትውልድ አሻራ ያረፈበት ትልቅ ታሪክ በመሆኑ እንዲጠናቀቅ ያለ ምንም ልዩነት በአንድነት መቆም ይጠበቅብናል" ብላለች።

የግድቡ ግንባታ ሲጀመር ኢትዮጵያዊያን ያሳዩትን ሕብረት አጠናክረው በመቀጠል ለግድቡ ድጋፋቸውን ሊያደርጉ ይገባል ነው ያለችው።

እርሷም በቀጣይ የሚጠበቅባትን አስተዋጽኦ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣ በቀጣይ ህዝቡም ይሁን መንግስት በግድቡ ላይ የሚኖራቸው አቋም አንድ አይነት ሊሆን ይገባል ብላለች።

"የኢትዮጵያ መንግስት የሚወስደው አቋም ምን ጊዜም የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብር መሆን ይኖርበታል" ስትልም አስተያየቷን ሰጥታለች።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ "የአገርንና የህዝብን ጥቅም የሚጎዳ" ማናቸውንም ድርድር እንዳማያደርግ አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም