ከአድዋ ድል አንድነትና አብሮነትን መማር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ከአድዋ ድል አንድነትና አብሮነትን መማር ይገባል
አክሱም፣ የካቲት 23/2012 (ኢዜአ) ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በአንድነትና አብሮነት የተጎናጸፉትን የአድዋ ድል መማር እንደሚገባ የተለያዩ ክልሎች ተወካዮች አመለከቱ።
ከሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የተወከሉ የህብረተሰብ ክፍሎች 124ኛ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በአድዋ ሰሎዳ ተራራ ግርጌ ደማቅ በሆነ ስነስርዓት በጋራ እያከበሩ ነው።
ተወካዮቹ ለኢዜአ እንዳሉት የአድዋ ድል በዓል ሲከበር አንድነትንና ህብረትን በሚያጠናክር መልኩ መሆን ይገባል።
ከአዲስ አበባ አስተዳደር የተወከሉት አርበኛ ባዩ ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት አድዋ ታሪካዊ ስፍራዎች ሲጎበኙ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል።
"ቀደምት አባቶች የሀገር ሉአላዊነት ላለማስደፈር በአንድ ሆነው ያስገኙት ድል በቀላል መታየት የለበትም" ብለዋል።
"እንደ አባቶቻችን አንድነት መማር ማሰተማር፣መግባባት እና ችግሮች በውይይት መፍታት ይገባል" ሲሉ ገልጸዋል።
ወጣቱ ፣ሰላም ፍቅር እና አንድነትን ከአድዋ ድል ልምድ መውሰድ እንዳለበትም አመለክተዋል።
ከአዲስ አበባ የዓድዋ ድልድይ ጀምሮ ውጫሌ፣ማይጨው፣እንዳየሱስ እና አድዋን በመጎብኘታቸው ትልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው የተናገሩት ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል የመጡት ወይዘሮ መስከረም መንበረ ናቸው።
"ህብረተሰቡ በየአካባቢው ያደረገላቸው አቀባበል በኢትዮጵያያን መካከል ፍቅር ፣አንድነትና ሰላም እንዳለ ያሳያል" ያሉት ወይዘሮ መስከረም ህዝቡ በልዩነት ሳይከፋፈል ሀገራዊ አንድነቱ ሊያጠናክር እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከአድዋ ድል ትምህርት በመውሰድ በአዲስ ወኔ የሀገሪቱን አንድነት የማስቀጠል ኃላፊነት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
"የሀገራችን ውስጣዊ ችግሮች በመረዳዳት እና በውይይት መፍታት ይገባል፣መልካም አስተሳሰብን ማዳበር ተገቢ ነው " ብለዋል።
ከደቡብ ክልል የተወከሉት አቶ ሰሎሞን ተስፋየ በበኩላቸው የአሁኑ ትውልድ ታሪኩን በማወቅ አዲስ የራሱ ታሪክ መስራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።
''አንድነታችን ለማስጠበቅ በትጋት እንሰራለን፣ልዩነታችን ደግሞ በመደማመጥና በውይይት ልንፈታ ይገባል'' ብለዋል።
የፖለቲካ ልዩነት መኖሩ በህሪያዊ ቢሆንም በሀገር ሉአላዊነት ጉዳይ ግን ሁሉም ለድርድር ሊያቀርበው እንደማይገባ ተናግረዋል።
"አንድነት ካለ ድል አለ፣ ድል ለማስመዝገብ ደግሞ በአንድነት እንቆማለን "ያሉት ደግሞ ከአማራ ክልል የተወከሉ አቶ አዝመራ በየነ ናቸው።
ሀገራዊ ስሜትና ብሄራዊ ማንነት የሚገለጸው አንድ ሀገር ሲኖር መሆኑን ጠቅሰው ሀገሪቱን በአንድነትና በሰላም አብሮ በመኖር ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንደሚገባ አንስተዋል።
በትግራይ ክልል የአድዋ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አብረሀት ግርማይ በበኩላቸው "የአድዋ ድል ትልቅ ትርጉም የሚኖረው አንድነታችንና ፍቅራችን ካጠናከርን ነው " ብለዋል።
መከፋፈልን የሚሰብኩ አካላት የኢትዮጵያ ህዝብ ሊታገላቸው እንደሚገባም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በቁጥር ከ200 የሚበልጡ የተለያዩ ክልሎች ተወካዮች ከአድዋ ድል ጋር ተያያዥነት ያላቸው ታሪካዊ ስፍራዎች ጎብኝተዋል።