የአድዋ ድል የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ድል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ድል ነው
አዲስ አበባ የካቲት 23/2012 (ኢዜአ) የአድዋ ድል የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ድል ነው ሲል የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ገለጸ።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለ124ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፏል።
የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ፥ የአድዋ ድል የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ድል ነው ብሏል።
የኦሮሞ ህዝብ በጦርነቱ እንደነበረው ጀግንነት ሁሉ ወደፊትም ለሀገሪቱ አንድነት የራሱን ድርሻ በመወጣት አሁን የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት መልእክት አስተላልፏል።
አድዋ የኢትዮጵያ ጀግኖች ክንድ ብርታት የታየበት ሜዳ መሆኑን ያወሳው መግለጫው፤ በተለይም ጥቁሮች ነጮችን ድል የመቱበትና መቼም የማይሻር ታሪክ ያኖሩበት ነውም ብለዋል።
በዚህ ጉልህ ስፍራ በሚሰጠው ታሪክ ውስጥ የነበሩ ጀግኖች ጥበብና የጦር ብልሃት ለሀገር ግንባታው የዋሉትን ታላቅ ተጋድሎ በመግለጫው ተጠቅሷል።
"አድዋ ድላችን ነው ስንልም በጦርነቱ የኦሮሞም ሆነ መላው የሀገራችን ህዝቦች ምን ያህል መስዋእትነት እንደከፈሉበት በመገንዘብ ነው" ያለው መግለጫው፤ ዛሬ የ124ኛው ድላችንን ስናከብርም በአንድነት፣ በጀግንነትና በአብሮነት የነገይቱን ሀገራችንን ለመገንባት ስንቅ እንዲሆነን ነው" ብሏል።
የኦሮሞና መላው የሀገራችን ህዝቦች የትናንት ድላችንን ስናወሳ አሁን የተያያዝነውን የለውጥ ጉዞን ለማሳካት በተባበረ ክንዳችን የድርሻችን እንወጣ ብሏል።