የአዲስ አበባ የኢማሞች ማህበር ተመሰረተ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ የኢማሞች ማህበር ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22/2012 (ኢዜአ) የመስጊድ ኢማሞች በሕብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ቀረቤታ ተጠቅመው በመቻቻልና በሰላም ዙሪያ ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አሳሰበ።
የአዲስ አበባ ከተማ የኢማሞች ማህበር በዛሬው እለት ተመስርቷል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢማሞች በህብረተሰቡ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ከፍተኛ ነው።
በመሆኑም ይህን ተቀባይነታቸውን በመጠቀም ስለ ሰላምና መቻቻል ሕብረተሰቡን በማስተማር ግንዛቤ መፍጠር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ለዚሁ ተግባራቸው ስኬታማነት መንግስትም ሆነ አጠቃላይ ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
በርካታ ኢማሞች ህዝቡን የሚያገለግሉት ያለ በቂ ክፍያ መሆኑን የጠቆሙት ሀጅ ዑመር መንግስት ለእነዚህ ኢማሞች የመኖሪያ ቤት ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ኢማሞች ማህበር ሰብሳቢ ሼህ ሙሃመድ ጠይብ ቀደም ባሉት ጊዜያት የመስጊድ ኢማሞች ልዩ ክብር እንደነበራቸው አስታውሰዋል።
ህብረተሰቡ ኢማሞቹ ለሚሰጡት ትምህርት ልዩ ትኩረት በመስጠት ይከታተል እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የኢማሞች ተቀባይነት እየተሸረሸረ በመምጣቱ ተሰሚነታቸውም በዚያው ልክ መውረዱን ይናገራሉ።
እንዳውም በአንዳንድ አካባቢዎች ኢማሞች የሚሰጡትን ትምህርት ላለመቀበልና ይባስ ብሎ የማጥላላትና የትንኮሳ ተግባራት እየተፈጸሙ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የእነዚህ ችግሮች መከሰት ዋናው ምክንያት ደግሞ ስለ ሰላምና መቻቻል እንዲሁም አንድነት በቂ የሚባል ትምህርት ባለመሰጠቱ እንደሆነ ይናገራሉ።
ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም የኢማሞች ማህበር መመስረት አስፈላጊ መሆኑን የማህበሩ ሰብሳቢ ተናግረዋል።
በመሆኑም ማህበሩ በዛሬው እለት ከ150 በላይ አባላትን ይዞ መመስረቱን ገልጸዋል።
በማህበሩ ምስረታ ላይ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትና መጋቤ ሀዲስ እሸቱ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።
በእለቱ ባስተላለፉት መልእክትም የመስጊድ ኢማሞች በአገራዊ አንድነትና መቻቻል ላይ ለሕብረተሰቡ ጠንካራ ትምህርት ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ያልተገቡ ድርጊቶች በአንዳንድ ሙስሊም ወገኖች ብቻ ሳይሆን በሌሎች የእምነት ተከታዮችም የሚስተዋሉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህንን ችግር ለማስወገድ ሁሉም የእምነት አባቶች ተከታዮቻቸውን ስለ ሰላም፣ መቻቻልና አብሮነት አብዝተው ማስተማር እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።
ከአባቶች የተገኙና የሚተላለፉ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችም ለየተከታዮቻቸው በአግባቡ ማድረስ ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በመቻቻልና በሰላም ዙሪያ እያሳዩት ላለው ትጋትና ቁርጠኝነት በማህበሩ ምስረታ ወቅት እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸው በተወካያቸው አማካኝነት ተቀብለዋል።